ዜና እረፍት |የቀድሞው የሻሸመኔ ከተማ አሰልጣኝ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወታቸው አለፈ

ሻሸመኔ ከተማን ከምስረታው ጀምሮ ለረጅም ጊዜያት ያሰለጠኑት አሰልጣኝ ደጀኔ ጫካ ትላንት ምሽት በድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው አለፈ፡፡

በሻሸመኔ ስፖርት ክለብ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠሩ እና በርካታ ታዳጊዎች ማፍራት ከቻሉ አሰልጣኞች መካከል የነበሩት አሰልጣኝ ደጀኔ ከ1970ዎቹ ጀምሮ በአካባቢው በሚገኙ ቡድኖች እና ለወረዳ እንዲሁም ለሀዋሳ ዱቄት ክለብ በተጫዋችነት ያሳለፉ ሲሆን ወደ አሰልጣኝነቱ ከመጡ በኃላ ትልቅ ስራዎች ሰርተው አልፈዋል። ሻሸመኔ ከተማን በ1990 መባቻ ጀምሮ መሠረት እንዲይዝ ያደረጉ ሲሆን ሻሸመኔ ከተማን ከኦሮሚያ ሊግ አንስቶ በብሔራዊ ሊግ እንዲሁም በ1999 ወደ ፕሪምየር ሊግ በማሳደግ ሁለት የውድድር ዘመናትን በሊጉ ማሳለፍ ችለው የነበረ ሲሆን እስከ 2004 መጨረሻ ድረስም ቡድኑን በአሰልጣኝነት መርተውታል።

ባለፉት አመታት ከእግርኳሱ ርቀው በንግድ ስራ ተሰማርተው ኑሯቸውን እየገፉ የነበሩት አሰልጣኝ ደጀኔ ጫካ ትላንት በሚኖሩባት ሻሸመኔ ምሸት 5:00 ላይ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ምክንያት በተወለዱ 50 አመታቸው ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። ባለትዳር እና የ3 ልጆች አባት የነበሩት አሰልጣኝ ደጀኔ ነገ ረፋድ በሻሸመኔ ቅዱስ ዮሀንስ ቤተክርስቲያን ስርአተ ቀብራቸው የሚፈፀም ይሆናል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ በአሰልጣኝ ደጀኔ ጫካ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቻቸው ለወዳጅ ዘመድ እና ለስፖርት ቤተሰቡ መፅናናትን እንመኛለን!