ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና አዳማን በማሸነፍ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል

የ26ኛው ሳምንት የመጨረሻ የሆነው እና በጉጉት የተጠበቀው የኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በቡና የ1-0 አሸናፊነት ተፈፅሟል።

በ25ኛው ሳምንት ጨዋታዎቻቸውን በድል ያጠናቀቁት ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ውስጥ ከአንድ በላይ ቅያሪ አላደረጉም። ኢትዮጵያ ቡና ከሶዶው ጨዋታ ባፒስታዬ ፋዬን ቀንሶ አስራት ቱንጆን ያስገባ ሲሆን አዳማም ኤሌክትሪክን ከረታበት ጨዋታ ከቅጣት የተመለለትን ዳዋ ሁቴሳን በቡልቻ ሹራ ምትክ ከመጠቀሙ በቀር ሌላ ለውጥ አላደረገም።

11፡45 ሲል የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንደተጠበቀውም ከፍ ያለ ፉክክር የተስተናገደበት ነበር። ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ጨዋታዉን የጀመሩበት ፍጥነት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የበላይ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ከእያሱ ታምሩ እና ሚኪያስ መኮንን የቡድኑ የግራ ወገን ጥምረት በመነሳት ወደ ውስጥ ይጣሉ የነበሩት ኳሶች ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ናቸው። ቡድኑ 9ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ ቀኝ የመከላከል ሳጥን ውስጥ ከአቡበከር ነስሩ እና ሳምሶን ጥላሁን ቅብብል የፈጠረው እና ንታንቢ ከርቀት የሞከረው ኳስ የመጀመሪያው አስፈሪ ጥቃት ነበር። 13ኛው ደቂቃ ላይም ከዚሁ ግራ መስመር እያሱ ታምሩ ያነሳው ኳስ በአቡበከር በግንባር ተገጭቶ በተከላካዮች ተመልሷል። ቀጣዮቹ 10 ደቂቃዎች ግን የኢትዮጵያ ቡና ጫና እየቀነሰ የሄደባቸው እና በምትኩም በጨዋታው መሀል ሜዳ ላይ የበረከቱ ፍትጊያዎችን እና የጨዋታ መቆራረጥን የተመለከትንበት ነበር። 

በከነዓን ማርክነህ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ የሚመስለው የአዳማ ከተማ የጨዋታ ሂደት መሀል ሜዳውን ማለፍ የቻለባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። በሱራፌል ዳኛቸው እና በረከት አዲሱ የሚመሩት ሁለቱ ኮሪደሮች ከከንዓን ጋር የነበራቸው የቅብብል መስመሮች ተቋርጠው ዳዋ ሁቴሳም ፊት ላይ ለብቻው ተነጥሎ ይታይ ነበር። ከሁሉም በላይ ቡድኑ ከራሱ ሜዳ መውጣት በቻለባቸው ጊዜያት የአማካይ ክፍል ተጨዋቾቹ ውሳኔዎች ከሜዳው ሁኔታ ጋር አብሮ አለመሄዱ በከፍተኛ ትኩረት ሲጫወቱ ለነበሩት የኢትዮጵያ ቡና የኃላ መስመር ተጨዋቾች ሲሳይ አድርጓቸዋል።  ከከንዓን ፣ በረከት እና ሱራፌል በተጨማሪም አዲስ ህንፃ ከሳንጋሪ ፊት በመጠጋት ለቡድኑ ማጥቃት ተጨማሪ ሀይል ለመሆን ቢሞክርም የቅብብሎች መቆራረጥ 31ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ከርቀት ከመታው ኳስ በቀር አዳማ በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም የጠራ የግብ ሙከራ እንዳያደርግ አስገድዶታል። 

ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ የተጋጣሚው የማጥቃት ኃይል መዳከሙን ተከትሎ ከፊት ያሰለፋቸውን ሶስት አጥቂዎች በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ እንዲቆዩ በማድረግ እና የመስመር ተከላካዮቹን እገዛም በመጨመር ይበልጥ ተጭኖ ተጫውቷል። 25ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳኑሚ ከአቡበከር በደረሰው ኳስ ሳጥን ውስጥ ከሱሊማን መሀመድ ጀርባ ገብቶ ከጃኮ ፔንዜ ጋር የተገናኘበት እንዲሁም በጭማሪ ደቂቃ አቡበከር ከሳጥን ውስጥ ሞክሮት ፔንዜ ያዳነበት ሙከራዎች ቡድኑ ከፈጠራቸው አጋጣሚዎች መሀከል ጎል ለመሆን የቀረቡት ነበሩ። 

ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑ ተደጋጋሚ የግራ እና ቀኝ ጥቃት ከፊታቸው ከሚገኙት አማካዮች ብዙ እገዛ የማያገኙትን የአዳማን የመስመር ተከላካዮች ሱሊማን መሀመድ እና አንዳርጋውቸ ይልሀቅ ስራ ከማብዛት ባለፈ በመጨረሻው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምትን ያስገኘም ነበር። ሚኪያስ መኮንን በግራ መስመር አታሎ ሲገባ በተሰራበት ጥፋት ነበር የፍፁም ቅጣት ምቱ የተሰጠው። በአዳማ ተጨዋቾች ተቃውሞ ያስነሳው እና ጃኮ ፔንዜን ለመጀመሪያ ቢጫ ካርድ የዳረገውን ይህን አጋጣሚ ሳሙኤል ሳኑሚ በአግባቡ ተጠቅሞ የጨዋታውን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል።

እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት አዳማ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ተነቃቅተው ገብተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ወደ ደረሱበት የኢትዮጵያ ቡና የመከላከል ቀጠናም ገፍተው ለመጫወት ችለው ነበር። 48ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ህንፃ ከሳጥን ውጪ ያደረጋት ሙከራም ሀሪሰንን ባትፈትንም የእንግዶቹ የመጀመሪያ ኢላማዋን የጠበቀች ሙከራ ነበረች። ከደቂቃዎች በኃላ ደግሞ ዳዋ ሁቴሳ የሱራፌልን መጎዳት ተከትሎ ተቀይሮ ከገባው ቡልቻ ሹራ ጋር አስገራሚ ቅብብል አድርጎ በቀኝ በኩል በመግባት የሞከረውን ኳስ ሀሪሰን እንደምንም አዳነበት እንጂ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር። የአዳማዎች ጫና በበረታባቸው እነዚህ ደቂቃዎች ግን ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ለመጠጋት ቢገደዱም በረጅሙ በሚጣሉት ኳሶች የሚሰነዝሯቸው መልሶ ማጥቃቶች ከበድ ነበሩ። በአመዛኑ ሚኪያስ መኮንንን እና አቡበከር ነስሩን መዳረሻ ካደረጉት ኳሶች መሀከል 50ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ እስከ አዳማ ሳጥን ድረስ ገብቶ የነበረበት የመልሶ ማጥቃት ሂደት ተጠቃሽ ነበር።  

በቀጣይ ደቂቃዎች አዳማዎች የሚሰነዘርባቸውን መልሶ ማጥቃቶች በመቋቋም በተቻላቸው መጠን በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል ላይ ለመቆየት ጥረታቸውን የቀጠሉባቸው ነበሩ። 62ኛው ደቂቃ ላይ ምኞት ደበበ ከመሀል ሜዳ ጠጋ ብሎ የመታው የቅጣት ምትም በግቡ ቋሚ የተመለሰበትን አጋጣሚ ተመልክተናል። በዛው መጠን ኢትዮጵያ ቡናዎችም 57ኛው ደቂቃ ላይ ከቶማስ ስምረቱ የግንባር ሙከራ አንድ ደቂቃ በኃላ አስደናቂ ብቃቱን ሲያሳይ ባመሸው ሙኪያስ መኮንን የግል ጥረት እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ችለው ነበር። ሚኪያስ በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን ኳስ በቀኝ በኩል ተከላካዮችን አልፎ ከገባ በኃላ ነበር  የሞከረው። በዚህ ሁኔታ ተጋግሎ የቀጠለው ጨዋታ 69ኛው ደቂቃ ላይ ለአዳማ ጥሩ ያልሆነ ክስተትን አስተናግዷል። ቢጫ የነበረበት የመስመር 

አማካዩ በረከት ደስታ በኤፍሬም ዘካርያስ ተቀይሮ እየወጣ ባለበት ሰዐት ዳኛውን ሀይለ ቃል በመናገሩ ሳይቀየር በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። የኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይህ ውሳኔም በአዳማ ተጨዋቾች በኩል ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ለፀብ እስከመጋበዝ የደረሰ ነበር።

በ10 ተጨዋቾች ለመቀጠል የተገደዱት አዳማዎች አሁንም ዕድሎችን ለመፍጠር መንቀሳቀሳቸው የቀጠለ ቢሆንም 81ኛው ደቂቃ ላይ ከንዓን ማርክነህ ካደረገው የርቀት ሙከራ ሌላ ተጨማሪ አደጋ መፍጠር አልቻሉም። ይልቁኑም 85ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ የመጨረሻ ሰው ሆኖ በአቡበከር ነስሩ ላይ ከሳጥን ውጪ በሰራው ጥፋት ሌላኛው የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኖ አዳማም ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት ውጤታማነት መንምኗል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው አክሊሉ ዋለልኝ እና ወንድይፍራው ጌታሁን የመሳሰሉ ተጨዋቾችን ቀይረው በማስገባት በጥንቃቄ መሪነታቸውን አስጠብቀው ጨዋታውን መጨረስ ችለዋል። በተመዘገበው ውጤት አዳማ ከተማ ሊጉን መምራት የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀም ወደ 5ኛ ደረጃ ሲወርድ አሸናፊው ኢትዮጵያ ቡና ከመሪው ጅማ አባ ጅፋር በሁለት ነጥቦች አንሶ ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ያስቻለውን ድል አግኝቷል።