ሩሲያ 2018 | ግብፅ (ፈርኦኖቹ)

የግብፅ ብሄራዊ ቡድን ከ28 ዓመታት ጥበቃ በኃላ ወደ ዓለም ዋንጫ ማለፍ ችሏል፡፡ ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም ወዲህ የነበረው ወርቃማ ትውልዷ ማሳካት ያልቻለውን ገድል በመሃመድ ሳላህ መሪነት ግብፅ ወደ ዓለም ዋንጫው ተመልሳለች፡፡

ፈርኦኖቹ የሚገኙበት ምድብ አንድ በንፅፅር ወደ ሁለተኛው ዙር የማለፍ ሰፊ እድልን እንዲሰንቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ሐሙስ ምሽት ሩሲያ ሳውዲ አረቢያ 5-0 አሸንፋ የዓለም ዋንጫው የተጀመረ ሲሆን በጨዋታ እንቅስቃሴ ግብፆች ሁለቱንም ሃገራት የማሸነፍ አቅም እንዳላቸው ያስገነዘበ ጨዋታ ነበር፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታ ከጋና ጋር 1-1 ከተለያየች በኃላ የውጤት ቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ግብፅ ተስፋ እና ስጋት እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

ተስፋ

አርጀንቲናዊው ሄክቶር ኩፐር የአሰልጣኝነት መንበሩን ከአሜሪካዊው ቦብ ብራድሊ ከተረከቡ ወዲህ ብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ መሻሻልን አሳይቷል፡፡ ይህ በአንድ አጋጣሚ የመጣ ክስተት አይደለም፡፡ ብዙ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል አንደኛው ብሄራዊ ቡድን ለ7 ዓመታት ርቆ ከቆየበት እና ባለሪከርድ አሸናፊ ወደሆነበት የአፍሪካ ዋንጫ መመለስ መቻሉ ነው፡፡ የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ መድረስ መቻላቸው ለዓለም ዋንጫው ጉዞ ማመር አይነተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ኩፐር የሚጠቀሙት መከላከል እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ውጤታማ አድርጓቸዋል፡፡ የተደረጃ የተከላካይ ክፍልም በወቅታዊ ሁኔታ ትንሽ ችግሮችን ቢታዩበትም ጥሩ መሆኑ ግን ለግብፆች ተስፋ ነው፡፡ ከጉዳቱ አገግሞ ለምድብ ጨዋታዎች ብቁ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ሳላህም ለቡድኑ ውጤት ማማር ቀጥተና ተፅዕኖ መፍጠር ይችላል፡፡ በቅርብ ሳምንታት ቡድኑ ከመከላከሉ ባሻገር ተጭኖ ለመጫወት የሚያደርገው ሙከራ ትንሽም ቢሆን መሻሻሎችን ማሳየቱ ጥሩ ጎን፡፡

የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 3 (1934፣ 1990 እና 2018)

ውጤት – ሁለት ግዜ የምድብ ተሳትፎ

ስጋት

ኩፐር ቡድናቸው የለሳላህ ጥርስ የሌለው አንበሳ መሆኑን በሚገባ ይረዱታል፡፡ ግብ ለማግኘት በአብዛኛው ሳላህ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ እና ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ማገገሙ አጠራጣሪ መሆኑ የግብፅ ስጋት ነው፡፡ የለሳላህ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴው አዋጪ አይመስልም፡፡ እነመሃሙድ ካራባ፣ አህመድ ሃሰን ኮካ፣ ማርዋን ሞሂሰን እና መሃሙድ ትሬዝጌ ኩፐር የሚከተሉት አጨዋወት ጋር የሚዋሃዱ አይመስልም፡፡ የአጥቂ ክፍሉ በአጠቃላይ ከሳለህ ውጪ ባለፉት አመታት ያስቆጠረው ግብ መጠን አነስተኛ ነው፡፡ ይህ የኩፐር የራስ ምታት ነው፡፡

ግብፅ ዛሬ ዩራጋይን በመግጠም የዓለም ዋንጫ ጉዞዋን ትጀምራለች፡፡

ሙሉ ቡድን

ግብ ጠባቂዎች

ሻሪፍ ኤክራሚ (አል አህሊ)፣ ኤሳም ኤል-ሃዳሪ (አል ታዎን/ሳውዲ አረቢያ)፣ መሃመድ ኤል-ሽናዊ (አል አህሊ)

ተከላካዮች

መሃመድ አብደል-ሻፊ (አል ፈታ/ሳውዲ አረቢያ)፣ አይመን አሻራፍ (አል አህሊ)፣ አህመድ ኤልሞሃመዲ (አስቶንቪላ/ እንግሊዝ)፣ አህመድ ፋቲ (አል አህሊ)፣ ኦማር ጋብር (ሎስ አንጀለስ ኤፍሲ/ዩናይትድ ስቴትስ)፣ አሊ ጋብር (ዛማሌክ)፣ መሃሙድ ሃምዲ (ዛማሌክ)፣ አህመድ ሄጋዚ (ዌስትብሮምዊች አልቢዮን/እንግሊዝ)፣ ሰዓድ ሳሚር (አል አህሊ)

አማካዮች

መሃመድ ኤልኔኔ (አርሰናል/እንግሊዝ)፣ አብደላ ኤል-ሳዒድ (አል ኢትሃድ ጅዳ/ሳውዲ አረቢያ)፣ ታሪቅ ሃምድ (ዛማሌክ)፣ ሳም ሞርሲ (ዊጋን አትሌቲክ/እንግሊዝ)፣ ሺካባላ (አል ራኢድ/ሳውዲ አረቢያ)፣ ረመዳን ሶብሂ (ሃድርስፊልድ ታውን/እንግሊዝ)፣ መሃመድ ሃሰን ትሬዝጌ (ካሲምፓሳ/ቱርክ)፣ አምር ዋርዳ (አትሮሚቶስ/ግሪክ)

አጥቂዎች

መሃመድ ሳላህ (ሊቨርፑል/እንግሊዝ)፣ ማርዋን ሞህሰን (አል አሃሊ)፣ ማሃሙድ ካራባ (አል ኢቲሃድ ጅዳ/ሳውዲ አረቢያ)