ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ| ለገጣፎ፣ ፌዴራል ፖሊስ እና መድን አሸንፈዋል

የኢትዮጽያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ሲጀምሩ ለገጣፎ፣ ፌዴራል ፖሊስ እና መድን አሸንፈዋል።

ለገጣፎ ላይ ኢኮስኮን ያስተናገደው ለገጣፎ ለገዳዲ በመጨረሻ ሰዓት በተቆጠረ ጎል 1-0 አሸንፎ ወጥቷል። ገሚሱ የሜዳ ክፍል በውሀ በመሞላቱን ለእንቅስቃሴ ፈታኝ የነበረ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ ኢኮስኮዎች የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። በለገጣ በኩህ በ21ኛው ደቂቃ ሱራፌል አየለ፣ በ30ኛው እና በ38ኛው ደቂቃ በፊት መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፋሲል አስማማው እንዲሁም በ42ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ፍቃዱ ያደረጓቸው ሙከራዋቹ ተጠቃሽ የነበሩ ሲሆን በኢኮስኮ በኩል በ25ኛው ደቂቃ የኋላሸት ሰለሞን፤ በ34ኛው አበበ ታደሰ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች በግብ ጠባቂው አንተነህ ሀብቱ የግል ጥረት ከሽፋባቸዋል። 

ከዕረፍት መልስ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ ለገጣፎዋች ተጭነው መጫወት ችለዋል። የሜዳውን ደረቃማ ክፍል የያዙት ኡኮስኮዋች በተቃራኒው በመከላከል ተጠምደው ታይተዋል። ወደፊት በቁጥር በዝተው የሚጠጉት ለገጣፎዎች በዛ ያለ የግብ ዕድብ የፈጠሩ ሲሆን በተለይም በሱፍቃድ ነጋሽ እንዲሁም ፋሲል ሞከረው የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው አጋጣሚ ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረቡባቸው ነበሩ። በ83ኛው ደቂቃ በሱፍቃድ ነጋሽ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ፋሲል አስማማው በግንባሩ በመግጨት ወደግብነት መለወጥ ችሏል። ጨዋታውም በለገጣፎ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሌሎች ጨዋታዎች ከድል ርቆ የነበረው መድን ወደ ቡራዩ አምርቶ ሚካኤል በየነ በ30ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል 1-0 አሸንፎ ሲመለስ ፌዴራል ፖሊስ በኦሜድላ ሜዳ ሱሉልታ ከተማን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። ወሎ ኮምቦልቻን ከሰበታ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ደግሞ ያለጎል ተጠናቋል።

በምድቡ ነገ ሁለት ጨዋታዎች ሲከናወኑ በ21ኛ ሳምንት ባህርዳር ከተማ ደሴን 1-0 እየመራ የተቋረጠው ጨዋታ ኦሜድላ ሜዳ ላይ በ4:00 ከቆመበት የሚቀጥል ይሆናል። ነቀምት ከአውስኮድ የሚያርጉት ጨዋታ ደግሞ የ24ኛ ሳምንት መደበኛ መርሐ ግብር ነው።