ሪፖርት| የዳኛችው በቀለ ሁለት ጎሎች ድሬዳዋን ከመውረድ አትርፈዋል

ትላንት በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የተቋረጠው የወልዋሎ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ እሁድ ረፋድ 4:30 ላይ ተካሂዶ ድሬዳዋ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ የቆየበትን የ2-0 ድል ማሳካት ችሏል።

ድሬዎች ከቅዳሜው ጨዋታ በተመሳሳይ 4-4-2 አደራደር ቢገቡም እንደ ትላንትናው የመሃል  አማካዬች ቦታ አያያዝ የጎንዮሽ ሳይሆን በሜዳው ቁመት የተሰደረ ነበር። በዚህም ኢማኑኤል ላርያ ለተከላካይ ቀርቦ በመጫወት ለተከላካዮች ሽፋን ሲሰጥ ዮሴፍ ዳሙዬ ደሞ ከአጥቂዎች ጀርባ በመገኘት እና የተጋጣሚን እንቅስቃሴ እና የኳስ አቅጣጫን በመከተል ወደ ሁለቱ ክንፎች እየወጣ በመጫወቱ የመሃል ክፍሉን እና የፊት መስመሩን ማገናኝት ችሏል። በዚህም ጨዋታው ከተቋረጠበት በተጀመረ በ4 ደቂቃ ውስጥ ተቀይሮ የገባው ዳኛቸው በቀለ ከማዕዝን የተላከችውን ኳስ በግርግር መሃል መትቶ ድሬዳዋን መሪ ማድረግ ችሏል።

አዶንጎ እና ከድር አንድ ሁለት ተቀባብለው ከድር መቶ ወደ ላይ ባወጣው ሙከራ የጀመሩት ባለ ሜዳዎቹ በመኩርያ ደሱ እና ወግደረስ ታየ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችም ማድረግ ችለው ነበር። እንግዶቹ በአንፃሩ ካስቆጠሩ በኋላ በተደጋጋሚ ስዓት ሲያባከኑ ወልዋሎዎች አቻ ለመሆን ተጭነው በመጫወት የግብ እድሎችም አምክነዋል። በተለይም እንየው ካሳሁን ያሻማውን ኳስ አዶንጎ በግሩም ሁኔታ መትቶ ያሬድ ዘውድነህ ተደርቦ ያወጣበት የሚጠቀስ ነው።

የመከላከል ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾች ቀይሮ በማስገባት በጥብቅ  በመከላከል  እና የ50/50 የአየር ኳሶች ማሸነፍ በሚችለው ዳኛቸው በቀለ መሰረት ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች መጫወት ምርጫቸው ያረጉት ድሬዎች ጥረታቸው ሰምሮ በ90+4ኛው ደቂቃ ላይ ለዳኛቸው በቀለ በረጅሙ የተላከውን  ኳስ የተስፋዬ ዲባባ ስህተት ታክሎበት ዳኛቸው እግር ደርሳ ሲመታት ቃሚውን መትቶ ሲመለስ ዳኛቸው በድጋሚ መትቶ ወደ ግብነት በመለወጥ የድሬዳዋን አሸናፊነት ማረጋገጥ ችሏል።

በውጤቱ መሠረት ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ መቆየቱ ሲረጋገጥ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ልዩነት የተበለጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አርባምንጭ እና ወልዲያን ተከትሎ ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርዷል።