አብርሀም መብራቱ ረዳቶቻቸውን አሳውቀዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ረዳቶቻቸውን ለፌዴሬሽኑ አሳውቀዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም ሁለት ምክትሎች የሚኖሩት ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ የቫዝ ፒንቶ ምክትል የሆኑትና ከዚህ ቀደም በማርያኖ ባሬቶ እና ዮሀንስ ሳህሌ ስር የዋልያዎቹ ምክትል አሰልጣኝ ሆነው ያገለገሉት ፋሲል ተካልኝ ወደ ብሔራዊ ቡድን ስራቸው የሚመለሱ ይሆናል። 

በአሰልጣኝነት ሁለተኛ የውድድር ዘመኑን ለመጀመር የተዘጋጀው ሙሉጌታ ምህረት ሌላው የአብርሀም ረዳት ነው። የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን አምበል በተጫዋችነት ዘመኑ ሁለት የሴካፋ ዋንጫን (አንዱን በአምበልነት) ከዋልያዎቹ ጋር ሲያሳካ በ2009 ከተጫዋችነት ተገልሎ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በሀዋሳ ከተማ የውበቱ አባተ ረዳት በመሆን ሲሰራ ቆይቷል።

በሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሲሰሩ የቆዩት አሰልጣኝ ውብሸት ደሳለኝ ለዋልያዎቹ ግብ ጠባቂዎች አስጣኝነት ተመርጠዋል። የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ የሆኑት ውብሸት በ1990ዎቹ አጋማሽ ዋልያዎቹ እና የኦሎምፒክ ቡድንን ግብ ጠብቀዋል። 

የአሰልጣኞቹ የቅጥር ስምምነት በቀጣይ ቀናት እንደሚጠናቀቅ ሲጠበቅ በቀጣይ ሌሎች ቅጥሮችም ይፈፀማሉ ተብሎ ይገመታል።