” ዕቅዴ ጠንካራ ቡድን መገንባት ነው” አብርሀም መብራቱ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ስለዝግጅት ጊዜያቸው ያላቸውን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል። 

ቡድኑ ዛሬ በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ካደረገው የመጀመሪያ ልምምዱ በኋላ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ስለእስካሁኑ የዝግጅት ጊዜ ጠቅለል አድርገው በሰጡት አስተያየት “እስካሁን በብሔራዊ ህክምና ኮሚቴ አማካይነት የተጫዋቾች ምርመራ ስናካሂድ ነበር። ያንን ጨርሰን ውጤቱን ካወቅን በኃላ ዛሬ በቀጥታ ሀዋሳ ገብተናል። ወደ ሆቴል ስንገባም ደስ በሚል መልኩ አቀባበል አድርገውልናል። የሆቴሉ የማናጅመንት አባላት እና የሀዋሳ ከተማ ስፖርት ቤተሰብ ለነበረው መልካም አቀባበል በቡድኑ ስም ከልብ አመሰግናለሁ። የመጀመሪያ ልምምዳችንን ዛሬ አድርገናል። አሁን ላይ የቡድኑ ስሜት እና ተነሳሽነት እንዲሁም የተጨዋቾች ጤንነት ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው። ይህ ደግሞ ለጅምራችን መልካም ነው።” ብለዋል።

በብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውስጥ ከሀገር ውጪ ከሚጫወቱ ተጨዋቾች በተጨማሪ በሀገር ውስጥ የሚጫወቱ የተወሰኑ ተጨዋቾችም በልምምዱ ላይ አለመገኘታቸውን አስመልክቶ አሰልጣኙ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። ” ከውጪ የሚመጡት ተጨዋቾች በኢንተርናሽናል ህግ መሰረት ነው ያልደረሱት። (በውድድር ላይ ስለሚገኙ) በተረፈ ሰምሶን አሰፋ በትራንስፖርት ችግር ምክንየት ከድሬዳዋ አልተነሳም ነበር። አዲስ ደግሞ ከህክምና በመመለሱ ነገ ልምምድ ይጀምረል። ጌታነህ ጀርመን በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ፌስቲቫል ላይ እየተካፈለ በመሆኑ ነው ያልተገኘው። ከንዓን ደግሞ የውጭ ዕድል አግኝቶ ነገ ስለሚጓዝ ነው ያልነበረው። ተጨዋቹ ሙከራውን ጨርሶ በቶሎ ከመጣ ቡድኑን ይቀላቀላል ብዬ አምናለሁ። ካልሆነ ግን ሌላ አማራጭ እንወስዳለን። ”

በመጨረሻም አሰልጣኙ ያላቸውን አጠቃላይ ዕቅድ በዚህ መልኩ አብራርተዋል “ዕቅዴ ጠንካራ ቡድን መገንባት ነው። እንደሚባለው ቡድኑ ከውጤት የራቀ ነው። እኔ ግን ጠንካራ ቡድን መገንባት ነው የመጀመሪያው አላማዬ። ነገር ግን በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ተሳታፊ ለመሆን እንጥራለን። እንደሚባለው የጋና ቡድን በሙስና ምክንያት ሊታገድ ይችላል። ለኛ ያ ይጠቅመናል ብለን ብናስብም የራሳችንን ስራ ሰርተን በምን መንገድ መሻገር አለብን የሚለውን ላይ ብቻ እናተኩራለን። ከሴራሊዮን ላለብን ጨዋታም በሚገባ ተጠናክረን እንቀርባለን።”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጳጉሜ 4 በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ሴራሊዮንን የሚገጥም ይሆናል፡፡