የኮፓ ኮካ ኮላ ሐገር አቀፍ ውድድር ተጀምሯል

የ2010 የኮፓ ኮካ ኮላ ሐገር አቀፍ ውድድር ቅዳሜ በባቱ ስታድየም በተደረገ ስነ-ስርዓት ተከፍቷል። 

በሀለቱም ፆታዎች 8 ክልሎች የሚሳተፉበት ይህ ውድድር ረፋድ ላይ የመክፈቻ መርሐ ግብሩ የተከናወነ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጊዜያዊ የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገ/ሥላሴ፣ የኮካ ኮላ የአፍሪካ ቀንድ ብራንድ ማናጀር ወ/ት ትዕግስት ጌቱ፣ የባቱ ከተማ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተውበታል። የመክፈቻ ንግግርም አድርገዋል። የየክልሎቹ የልዑካን ቡድን አባላት በባህላዊ ሙዚቃዎች ታጅበው በሰልፍ ከተመልካች የተዋወቁበት መርሐ ግብርም የመክፈቻው አካል ነበር። 


ከመክፈቻው ስነ-ስርዓት ቀጥሎ የባቱ ስታድየም ስታድየም በዝናብ ምክንያት ውሀ በማዘሉ አራት ጨዋታዎች በባቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከናውነዋል። በወንዶች ምድብ ሀ 5:00 ላይ ኦሮሚያ ክልል ከአማራ ክልል ባደረጉት ጨዋታ አሸብር ደረጄ ገና በሶስተኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ኦሮሚያ 1-0 አሸንፏል። 10:00 ላይ ድሬ ዳዋ  ከአፋር ባደረጉት ጨዋታ ደግሞ ልዑል መኮንን በ29ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ድሬ 1-0 መርታት ችሏል።


በሴቶች 6:30 ላይ ድሬዳዋ ከአፋር 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። ሀምዲያ መሐመድ በ18ኛው፣ በዓምላክ ገረመው በ40ኛው ደቂቃ ለድሬ ሲያስቆጥሩ መርሐዊት ተክላይ በ13ኛው ደቂቃ፣ ቤተልሄም ሳሙኤል በ19ኛው ደቂቃ የአፋርን ጎሎች አስቆጥረዋል። 8፡00 ላይ ኦሮሚያ አዲስ አበባን 3-1 አሸንፏል። አናንያ ደምሴ በ44ኛው፣ መካ ዓሊ በ45ኛው እንዲሁም ትዕግስት መንግስቱ በ80ኛው ደቂቃ የኦሮሚያን ጎሎች ሲያስቆጥሩ ስንታየሁ ዓለማየሁ በ54ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባን ብቸኛ ጎል አስቆጥራለች። 


የእሁድ ጨዋታዎች 
(ሁሉም ባቱ ስታድየም ላይ ይካሄዳል)

ሴቶች

03:00 ጋምቤላ ከ አማራ

05:00 ሐረሪ ከ ደቡብ

ወንዶች

08:00 ሐረሪ ከ ጋምቤላ

10:00 ደቡብ ከ አዲስ አበባ