“ትምህርት የወሰድንበት ጨዋታ ነው” የሴራሊዮን አሰልጣኝ ጆን ኪስተር

የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሸ ቀናት ሲደረጉ የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ሀዋሳ ላየ ኢትዮጵያን ገጥሞ 1-0 በመሸነፈ የምድቡ መሪ የመሆን እድሉን አምክኗል። 

ብሔራዊ ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ በዋልያዎቹ ብልጫ ተወስዶበት የታየ ሲሆን ሊጠቀስ የሚችል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ሆነ ሙከራ ሳያደርጉ ወጥተዋል። ሆኖም የቡድኑ አሰልጣኝ ጆን ኪስተር ከጨዋታው ትምህርት እንደወሰዱ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል። ” በዛሬው ጨዋታ ሽንፈት ብናስተናግድም ትምህርት የወሰድንበት ጨዋታ ነው። ከዚህ ጨዋታ መነሻነት ወደ ሜዳችን ተመልሰን ለጋናው ጨዋታ የምንዘጋጅ ይሆናል። በጨዋታው የፍፁም ቅጣት ምት ስለተሰጠብን ቅሬታ አላቀርብም። ስለዳኞች አስተያየት መስጠትም አልፈልግም። ውጤቱን ተቀብለን በቀጣይ ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ መዘጋጀት ነው ያለብን። ” 

አሰልጣኝ ጆን ኪስተር ለሽንፈታቸው እና ለደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው የቡድኑ ትልልቅ ተጫዋቾች እንደፈለጉት አለመሆናቸውን ምክንያትም አድርገዋል። ” ትልልቆቹ ተጨዋቾቼ እንዳላቸው ልምድ የሚጠበቅባቸውን ያህል አልተንቀሳቀሱም። ይህ አበሳጭቶኛል። ለቀጣዩ ጨዋታ ይህንን ችግር በመቅረፍ የተሻልን ሆነን እንደምንቀርብ ግን አስባለው።” ብለዋል። 

የምድቡ ሶስተኛ ጨዋታዎች በመስከረም ወር መጨረሻ ሲቀጥል ሴራሊዮን ከጋና፣ ኢትዮጵያ ከኬንያ የሚፋለሙ ይሆናል።