ካሜሩን 2019 | አህመድ ረሺድ እና ቢኒያም በላይ ስለዛሬው ጨዋታ ይናገራሉ

ዋልያዎቹ በሁለተኛው የምድባቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ሴራሊዮንን 1-0 አሸንፈዋል። አህመድ ረሺድ እና ቢኒያም በላይም ስለጨዋታው ያላቸውን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ከጋናው የሰፊ ግብ ሽንፈት በኋላ በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ስር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ዋልያዎቹ ዛሬ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ ከቻሉ ተጨዋቾች መካከል ደግሞ አህመድ ረሺድ እና ቢኒያም በላይ ተጠቃሽ ናቸው። የግራ መስመር ተከላካዩ አህመድ በጨዋታው ስላሳየው ትጋት እና ስለ አጠቃላይ የቡድኑ ጥንካሬ ከሶከር ኢትዮጵያ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ ” ጨዋታው አሪፍ ነበር። እንዳሰብነውም ወሩን ሙሉ የሰራነውን ነገር ከአላህ ጋር አሳክተነዋል። በግሌ ለማገለግለው ክለብ ያለኝን ነገር ሙሉ ለሙሉ አውጥቼ መስጠት እፈልጋለው። ዛሬ ደግሞ ለሀገሬ ነው የተጫወትኩት። ሀገሬ ከኔ ብዙ ትጠብቃለች። ስለዚህም የምችለውን መስዋትነት ከፍያለው። ብሔራዊ ቡድኑ እንደሌላው ጊዜ የተናጠል አልነበረም ፤ በአንድ አይነት ህብረት ነበር የምንጫወተው። ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ መስርተን ነበር የምንጫወተው። ይህም አሰልጣኛችን የሰጠንን ነገር በአግባቡ በመስራታችን የመጣ ይመስለኛል። ጨዋታው ለቀጣዩ የኬንያ ጨዋታም ትልቅ የቤት ስራን የሚሰጠን ነው። ያለብንን ክፍተት አርመን ጥንካሪያችንን ደግሞ አስቀጥለን በኬንያው ጨዋታ ላይ የምንጠቀመው ይሆናል። ” ብሏል።

በአልባንያው ስከንደርቡ እየተጫወተ የሚገኘው እና መስከረም ሶስት የሚሞሸረው አማካዩ ቢኒያም በላይም በጨዋታው ላይ ጥሩ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ ሌላኛው ተጨዋች ሆኗል። አማካዩ ስለዛሬው የቡድኑ ጥንካሬ እና ስለቀጣዩ ጨዋታ የሰጠው አስተያየይ ” ጨዋታው በጣም አሪፍ ነበር። ተነጋግረን ነበር የገባነው ፤ አሰልጣኛችን የሰጠንን ታክቲክ ተግብረነዋል ብዬ አስባለው። ኳስ ይዘን ለመጫወት ነበር ያሰብነው። ያንንም አድርገናል። በዚህም ምክንያት ተጋጣሚዎቻችን ብዙ እንዲሮጡ አድርገናቸዋል። በሰፊ ውጤት ተሸንፈን በመጣታችን ይህን ታሪክ የመቀየር ትልቅ ጉጉት ውስጣችን ነበር። ያም ጉጉት ይመስለኛል ብዙ ኳሶችን እንድንስት ያደረገን። ከዚህ የተሻለ ለመስራት በግልም በቡድንም መሻሻል ይኖርብናል። በቀጣይ ማረም የሚገባንን ነገር ከአሰልጣኛችን ጋር በመነጋገር በኬንያው ጨዋታ ላይ ተሻሽለን እንቀርባለን። እኛ የምንጫወተው መርሀ ግብሩን ለማሟላት ሳይሆን ያለፈውን ታሪክ ለመቀየር እስከሆነ ድረስ ከእግዚያብሔር ጋር እናልፋለን ብዬ አስባለው። ለዓዲስ ዓመት ለህዝባችን ጥሩ ስጦታ ሰጥተናል። በግሌም ድሉ ፣ አዲስ ዓመት እና ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚደረገው የጋብቻ ሥነስርዓቴ መገጣጠም እጅግ በጣም አስደስቶኛል። ” የሚል ነበር።

የአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ስብስብ በግብ ልዩነት የምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኝ እንጂ በነጥብ ከተፎካካሪዎቹ ጋር ተስተካክሎ ኬንያን ለማስተናገድ የአዲሱን ዓመት የመጀመሪያ ወር መገባደጃ የሚጠብቅ ይሆናል።

error: