ሴቶች ዝውውር | አዳማ ከተማ ሶስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

አዳማ ከተማ የሴቶችን እግርኳስ ለመቆጣጠር ያለመ እንቅስቃሴ ማድረጉን ቀጥሏል። ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከዚህ ቀደም ያስፈረመው ክለቡ ተጨማሪ ሶስት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ መቀላቀሉን አስታውቋል። 

በደደቢት የተከታታይ ዓመታት ጥንካሬ ውስጥ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ሶስት ተጫዋቾች ናቸው በሁለት ዓመት ኮንትራት ወደ አዳማ ያመሩት። የአጥቂ አማካይዋ ሰናይት ቦጋለ መልካም የውድድር ዓመት ያሳለፈች ሲሆን በኢቢሲ የዓመቱ ኮከቦች የመጨረሻ እጩዎች ውስጥ መካተት ችላለች። ሌላዋ ወደ ቡድኑ ያመራችው አንጋፋዋ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ወይንሸት ፀጋዬ ናት። ኦሌምቤ በሚል ቅፅል ስም ይበልጥ የምትታወቀው ወይንሸት በደደቢት ሁለተኛ አምበል ነበረች። በመሀል እና የቀኝ መስመር ተከላካይነት የምትጫወተው መስከረም ካንኮ ሌላዋ የቡድን አጋሮቿን ተከትላ ወደ አዳማ ለመቀላቀል የተስማማች ተጫዋች ናት። 

የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ እየታየበት ባለው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የዝውውር መስኮት አዳማ ከተማ እስካሁን 10 ተጫዋቾችን በማስፈረም ቀዳሚነቱን ይዟል።