ደደቢት የኤፍሬም ጌታቸውን ዝውውር አጠናቀቀ

በዝውውር መስኮቱ መጀመርያ ወደ ደደቢት ለማምራት ተስማምቶ የነበረው ኤፍሬም ጌታቸው ከመልቀቂያ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ዝውውሩ ተጓቶ ቆይቶ በመጨረሻም ሰማያዊዎቹን መቀላቀሉ ተረጋግጧል።

ከዚህ ቀደም በደደቢት ወጣት ቡድን የተጫወተው የመሐል ተከላካዩ ኤፍሬም ያለፉትን ሶስት የውድድር ዓመታት በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የቆየ ሲሆን ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ከነበሩ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ የነበረ ቢሆንም በ2010 ከጉዳት ጋር በተያያዘ ብዙም ግልጋሎት ሳይሰጥ ቆይቷል። ኤፍሬም መልቀቂያውን ከወልዋሎ በመውሰዱ ለደደቢት የፈረመው አሁን ቢሆንም ቀደም ብሎ ተስማምቶ የነበረ በመሆኑ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ከቡድኑ ጋር ሲሰራ ከመቆየቱ በተጨማሪ በትግራይ ዋንጫ ላይም ለደደቢት ሲጫወት እንደነበር ይታወቃል።