ከፍተኛ ሊግ | አክሱም ከተማ አራት አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርሟል

ላለፉት ዓመታት በ ከፍተኛ ሊጉ ላለመውረድ ሲታገል የነበረው አክሱም ከተማ ባለፈው ዓመት ያሳየውን መሻሻል በማስቀጠል በሊጉ ለመፎካከር በዝውውር መስኮቱ መሳተፍ ጀምሯል። የአራት ተጫዋቾችን ዝውውርም ማጠናቀቅ ችሏል። 

በ2007 ወደ ወልዋሎ አምርቶ ከተጫወተበት ጊዜ ውጭ ሙሉ የእግርኳስ ህይወቱን በመቐለ ያሳለፈው ኃይሉ ገብረየሱስ በዚህ ዓመት ከመቐለ ጋር መለያየቱን ተከትሎ ወደ አክሱም ከተማ አምርቷል። ለሶስተኛ ጊዜም ከአሰልጣኙ ጌታቸው ዳዊት ጋር የሚገናኝ ይሆናል።

ሌላው ለአክሱም የፈረመው የመስመር ተከላካዩ ዳዊት ዕቑበዝጊ ነው። ተጫዋቹ በሁለት ተከታታይ ዓመታት ወልድያ እና መቐለ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድጉ የቡድኖቹ አባል የነበረ ሲሆን ከዚህ በፊት ለመቐለ ሰባ እንደርታ፣ ወልዋሎ እና ወልድያ ተጫውቷል። እንደ ኃይሉ ሁሉ ለሁለተኛ ጊዜ የቀድሞ አሰልጣኙን የሚያገኝም ይሆናል።

ግብ ጠባቂው ሙሴ ዮሃንስ አክሱምን የተቀላቀለ ሌላው ተጫዋች ነው። ባለፈው ዓመት መጀመርያ መቐለ ሰባ እንደርታን ተቀላቅሎ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሽረ በውሰት ውል ያመራው ሙሴ ከመቐለ ጋር ያለው ውል በመጠናቀቁ ወደ አክሱም ማምራቱ ለማወቅ ተችሏል።

የክለቡ አራተኛ ፈራሚ ግብ ጠባቂው ጁቤድ ኡሞድ ነው። ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተገኘው ግብ ጠባቂ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ሆኖ ያሳለፈ ሲሆን በትግራይ ክልል ዋንጫ ምርጥ ብቃቱ ማሳየቱን ተከትሎ በቋሚነት አክሱምን መቀላቀል ችሏል።

error: