ሽመልስ በቀለ ታሪክ ለመስራት ይጫወታል

በዘንድሮ የግብፅ ሊግ በሰባት ጎሎች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በመምራት ላይ የሚገኘው ሽመልስ በቀለ የፔትሮጀት የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ለመሆን ዛሬ ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካዩ ሽመልስ በቀለ ለአምስት ዓመታት ለግብፁ ፔትሮጀት ወጥ አቋም በማሳየት እየተጫወተ ይገኛል። ምንም እንኳን ክለቡ ፔትሮጀት እንደ ቡድን ያለፉትን ዓመታት ውጤታማ መሆን ሳይችል ቢቀርም ሽመልስ በግሉ በተለይ በዘንድሮ የውድድር ዓመት አንፀባራቂ ጉዞ በማድረግ የሊጉን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በመምራት ላይ ይገኛል።

ሊጉ በግብፅ ዋንጫ (የጥሎማለፍ ዋንጫ) ምክንያት ለአንድ ሳምንት ከተቋረጠ በኋላ ዛሬ ከ12ኛ ሳምንት ሲቀጥል ፔትሮጀት በሜዳው ምሽት 01:00 ላይ ምስር አልማቃሳን ያስተናግዳል። በ34 ጎሎች የፔትሮጀት የምንግዜም ኮከብ ጎል አስቆጣሪነትን ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ እየተከተለ የሚገኘው ሽመልስ በቀለ በዛሬው ጨዋታ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር የሚችል ከሆነ በ36 ጎል የፔትሮጀት የምንግዜውም ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ታሪክ ሲሰራ አንድ ጎል ማስቆጠር ከቻለ ደግሞ የኮከብ ጎል አስቆጣሪነቱን በ35 ጎል የሚጋራ ይሆናል። የፔትሮጀትን የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን ግብፃዊው አላ ኢብራሒም በ35 ጎሎች እየመራ መሆኑ ይታወቃል።

ሽመልስ ከፔትሮጀት ጋር የውል ዘመኑ ማብቂያ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት በቀጣይ ጊዚያት በዛው ይቀጥላል ወይስ ወደ ሌላ የግብፅ ክለብ ያመራል አልያም ወደ ሌላ ሀገር በማቅናት የፕሮፌሽናል የእግርኳስ ህይወቱን ይቀጥላል የሚለውን በቅርቡ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።