የሚያስገርም ፍቅር ነው ያየሁት፤ በጣም አመሰግናለሁ – አሳሞአ ጂያን

የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ አምስተኛ የምድብ ጨዋታ በሳምንቱ መጨረሻ ተካሂደው ኢትዮጵያ በጋና በሜዳዋ 2-0 ተሸንፋ ወደ ካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሏ “የማይቻል” በሚመስል መልኩ ሲጠብ ጥቋቁር ከዋክብት ደግሞ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ከጫፍ ደርሳለች። በጨዋታው እንደሚሰለፍ ተጠብቆ የነበረውና ሙሉውን ክፍለ ጊዜ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ ያሳለፈው አምበሉ አሳሞአ ጂያን ስለ ጨዋታው እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያተሾመ ፋንታሁን ጋር ቆይታ አድርጓል።  

በቅድሚያ እንኳን ደስ አለህ፡፡

አመሰግናለው፡፡

ጨዋታው እንዴት ነበር? ሜዳው፣ ደጋፊው በአጠቃላይ እንዴት አገኘኸን?

በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር፡፡ ደጋፊው እንዳየኸው ግልብጥ ብሎ ቡድኑን ለመደግፍ መጥቷል። ይህ ከሜዳህ ውጭ ከባለሜዳ ጋር ስትጫወት ሁሌም ያለ ነው፡፡ ሜዳውም ትንሽ አስቸግሮን ነበር፤ የለመድነውን ረዥም ኳስ መጫወት አልቻልንም። ነገር ግን የምንፈልገውን ሶስት ነጥብ ይዘን ተመልሰናል፡፡ ነጥቡ በጣም ያስፈልገን ነበር። እሱን አሳክተናል። የኢትዮጵያ ቡድን ኳስ በመያዝ በጣም ጥሩ ናቸው፡፡ እኛ ደግሞ ልምድ አለን፤ ልምዳችንን ተጠቅመን አሸንፈናል። ዛሬ የነበረው ልዩነት የኛ ልምድ ነው፡፡ 


በጨዋታው ዋዜማ ለፕሬዝዳንታቸው ቡድኑን ወክለህ ቃል ስትገባ ነበር፣ ከልምምድ በኋላ በጋራ ስትዘምሩ ፊት አውራሪ ነበርክ። ዛሬም ወደ ስታዲየም ስትመጡ ቡድኑን እያነሳሳህ ስታዘምር ነበር፤ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ከአሰላለፍ ውጭ ነበር። ምክንያቱ ህመም ወይስ?

እንደቡድኑ አምበል እንዲሁም በቡድኑ ውስጥ ልምድ እንዳለው ተጫዋች ወጣቶቹን የመደገፍና የማበረታታት ኃላፊነት አለብኝ፡፡ ተጫዋቾቹ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የኔ እና አንድሬ (አዬው) ዓይነት ተጫዋቾች ልምድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሁላችንም ረዥም ርቀት ተጉዘን ነው የመጣነው። ከኬንያ ዝግጅት አዲስ አበባ የገባነው ትናንትና ጠዋት ነው፡፡ ልምምድ ለመስራት ወደ አዲስ አበባ ስንመጣም ሳናርፍ ነው የመጣነው፡፡ የአካል ድካም ስለነበረብን ልጆቹን በአእምሮ ማዘጋጀት ያስፈልግ ነበር፡፡ በአእምሮ ይበልጥ የተዘጋጀን ሆነን መቅረብ ያስፈልገን ነበር፤ ያን ደግሞ ማድረግ የኔ ኃላፊነት ነበር እሱን ነው ሳደርግ ያየኸኝ፡፡

ስለዚህ በቡድኑ ውስጥ የተያዝከው ለሥነ-ልቦና እንጂ ለመጫወት አልነበረም ማለት ነው?

በፍጹም አይደለም፤ የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው፡፡ እኔ በቡድኑ ውስጥ አለሁ። በቡድኑ ውስጥ እስካለው ድረስ ለመጫወት ዝግጁ ነኝ። ነገር ግን ማሰለፍ ወይም አለማሰለፍ የኔ ሳይሆን የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው፡፡ ማን ይጫወት ወይም ማን ይቀመጥ የአሰልጣኛችን ውሳኔ ነው፡፡ በዛሬው ጨዋታ ለአሰልጣኙ ዕቅድ ከኔ ይልቅ ሌላ ተጫዋች ይበልጥ ያስፈልገው ነበር ስለዚህም አልተጠቀመኝም፡፡ ከባለሜዳ ጋር እየተጫወትክ በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ጎል አግብተህ ከመራህ በኋላ ተጨማሪ አጥቂ ወደ ሜዳ የምታስገባው ምን ለመፍጠር ነው? አሰልጣኙ ታላቅ አሰልጣኝ ነው። ማድረግ የፈለገውን ነገር በፈለገው ሰዓት አሳክቷል፡፡ ወጣቶቹም ቢሆን የታዘዙትን ነገር በሰዓቱ አድርገዋል፡፡

የመጀመሪያዎቹን 20 ደቂቃዎች በሚገባ ከተጫወታችሁ በኋላ እንቅስቃሴያችሁ ወርዷል። እንደውም በሁለተኛው ግማሽ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ተበልጣችሁ ነበር። ሙሉ በሙሉ ኳሱን ለኢትዮጵያ ቡድን ሰጥታችሁ ወደመከላከል ገባችሁ?

በፍጹም “መስጠት” በሚለው አልስማማም፡፡ የጨዋታ ዕቅዳችን የነበረው በቻልነው አቅም ጨዋታውን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መጨረስ ነበር፤ ተሳክቷል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ኳስን ይዞ ከሚጫወት ቡድን ጋር ስትጫወት የምትፈልገውን ነገር በሚገባ ማወቅ ይጠበቅብሃል፡፡ የኛም ዓላማ በቻልነው አቅም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አግብተን ወደመደበኛ ጨዋታ መመለስ ነበር፤ አሳክተናል፡፡ እንደማሰበው የናንተም ቡድን ልጆች በሚገባ ይተዋወቃሉ። ለረዥም ጊዜ አብረው እንደተጫወቱ ያስታውቃሉ፣ ኳሷን መያዝ ያውቁበታል፣ በታክቲክና በዕቅድ ግን እኛ የተሻልን ነበርን፡፡ በጨዋታው መጀመሪያ ሁለት ጎሎች አግብተን ሳንደክም ጨዋታውን ጨርሰን ወጥተናል፡፡


የብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ካቆምክ በኋላ ነው የተመለስከው። አሁንስ በአፍሪካ ዋንጫው እናይሃለን?

የተመለስኩበት ምክንያት የሃገር ጥሪ ነው። ሃገሬ በፈለገችኝ ግዜ ሁሉ እምቢ ማለት አልችልም። አሰልጣኙ ግያን ምን ማድረግ እንደሚችል ያውቃል። ስለዚህም ጥሪ አደረገልኝ መጣሁ። እቆያለው ወይም አቆማለው አላውቅም። ወላድ በድባብ ትሂድ ጋና በጥበብ የተሞሉ አያሌ ታዳጊዎች አሏት።

ጋና፣ እንግሊዝ፣ አቡዳቢ፣ ቱርክ… ቀጣይስ ወዴት ነው?

የኔ ሥራ መጫወት ነው። ማኔጀሬ ምን ሰርቶ ሊበላ ነው እኔ መጪውን ክለብ የማስበው? የት እንደምሄድ አላውቅም። ጠረጴዛ ላይ የሚቀርበውን ማየት ነው። 

ኳስ ስለማቆም እያሰብክ ነው?

በፍጹም! እድሜህ ሲገፋ አቅምህ ሲደክም ማሰብህ አይቀርም። ነገር ግን አሁን ኳስ ስለማቆም አላስብም

ኢትዮጵያን እንዴት አገኘሃት?

የመጀመሪያዬ አይደለም። በተደጋጋሚ በአዲስ አበባ በኩል አልፋለሁ። ቆኝጆ ሃገር ናት፤ በርግጥ ከሆቴል ውጭ ብዙ ተዟዙሬ አላየኋትም። ያየኋትን ያህል ግን ምርጥ ህዝብ ያላት ምርጥ ሃገር ናት።

ስለህዝቡ ካነሳህ አይቀር ደጋፊው በተነሳህ በተቀመጥክ ቁጥር ሲጮህልህ ነበር ምን ተሰማህ?

የእውነት የሚገርም ፍቅር ነው ያየሁት። ከአየር መንገድ ጀምሮ፣ በሆቴል ከዛም ትናንት እንደገና ዛሬም… በጣም አመሰግናለው። ልዩ ፍቅር ነው ያየሁት።

በ2010 የዓለም ዋንጫ ስላመከንከው የፍፁም ቅጣት ምት ሳላነሳብህ ብንለያይ ሰው ምን ይለኛል?

የቱ ፍፁም ቅጣት ምት? እኔ ያኔ ነው የረሳሁት። እሱን ባልረሳ እስካሁን መጫወት አልችልም ነበር። ወደፊት ነው እንጂ እንዴት ወደኋላ ተመልሼ እሱን ላስብ እችላለው? ከዛ በኋላ ስንት ፍፁም ቅጣት መረት መትቼ አግብቻለው፤ ለምን እሱን አስባለው።

በመጨረሻ ለኢትዮጵያውያን የምታስተላልፈው መልዕክት…?

ለአቀባበላችሁ በጣም እናመሰግናለን