በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ያተኮረ ውይይት በአዳማ ተከናወነ

የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጋራ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ያዘጋጁት የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማው ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል የስፖርት ጋዜጠኞች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

ሙሉ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የኢፌዴሪ ስፓርት ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ርስቱ ይርዳውን ጨምሮ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደረሽን የስራ አስፈፃሚ አባላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የመክፈቻ ንግግር በማድረግ የውይይት መድረኩን የከፈቱት የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው እግርኳሱ በአሁኑ ወቅት ከሳምንት ሳምንት በጉጉት ከመናፈቅ ይልቅ ለሰዎች የስጋት ምንጭ እየሆነ መምጣቱን አውስተው ይህንን በስፓርቱ ላይ አሉታዊ ገዕታ እየፈጠረ የሚገኘውን ይህን የስፓርታዊ ጨዋነት መጎደል ችግርን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚወጡት ድርሻ የላቀ በመሆኑ ይህንን የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት መታሰቡን ገልፀዋል፡፡

በመቀጠል ለውይይት መነሻ እንዲሆን በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ሳሙኤል ስለሺ እና በሌሎች 9 የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በጋራ የተዘጋጀ ጥናታዊ ፅሁፍ በአቶ ስለሺ ለእድምተኞች ቀርቧል፡፡ ዘርዘር ያሉ ጉዳዮች በተዳሰሱበትና “ስፓርታዊ ጨዋነት፣ የተመልካች ረብሻ ሁከትና ብጥብጥ በኢትዮጵያ ወቅታዊ እግርኳስ” በተሰኘ ርዕስ በቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ የቀረቡት ዐቢይ ጉዳዮችን በሶስት መሠረታዊ ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበ ነበር፡፡

በፅሁፎ የመጀመሪያ ክፍል የጥናት ቡድኑ በአሁኑ ወቅት እየታዩ ባሉት የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግሮች መንስዔ ናቸው ያላቸውን ሀሳቦች በሶስት ክፍሎች በመክፈል ለመዳሰስ ተሞክሯል ፤ በዚህም ውስጥ እግርኳሳዊ ሙስና፣ ብሔርተኛ ክለቦች መበራከት እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዋነኝነት በጥናት አቅራቢው እንደ መንስዔነት ተጠቅሰዋል፡፡

በመቀጠልም በጥናታዊ ፅሁፉ የተዳሰሰው ጉዳይ ለእነዚህ መንስዔዎች በአቀጣጣይነት የጥናቱ ቡድኑ አገኘኋቸው ያላቸውን ሶስት አቀጣጣይ ምክንያቶችን አመላክቷል። እነዚህም የሜዳ ውስጥና ውጪ ያሉ ምክንያቶች እንዲሁም የስፖርት ሚዲያ እና መገናኛ ብዙሀን በሚል ሶስት ጥቅል አቀጣጣይ ምክያቶች ቀርበዋል፡፡ ከሜዳ ውጪ ባሉ ምክንያቶች ውስጥ መጠጥና እና ተያያዥ አደንዛዥ ዕፆች በስታዲየም ዙርያ መሸጥን ጨምሮ የፀጥታ ኃይል የተመለከተና ሌሎች ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን በሜዳ ውስጥ ምክንያትነት ደግሞ የዳኞችና ኮሚሽነሮች እንዲሁም የተጫዋቾችና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ቀርበዋል። የተጋነኑ ዘገባዎች፣ ለአካባቢ ቡድኖች ጥብቅና መቆም እና መሰል ምክንያቶች ደግም በመገናኛ ብዙሀን አቀጣጣይ ምክንያቶች ተብለው ቀርበዋል፡፡

በጥናታዊ ፅሁፍ የመጨረሻ ክፍል ደግሞ በአጭር በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ውስጥ ሊከወኑ የሚገባቸውን የማስፈፀሚያና የመተግበሪያ ኃሳቦችን ለመዘርዘር ተሞክሯል ፤ በዚህም ጥናት አቅራቢው አፅንኦት የተሰጣቸው ነጥቦች የህግ ማዕቀፍና የሰነዶች ዝግጅት እንዲሁም በጊዜ ሂደት ተከፍፈለው የሚከወኑ የአዳዲስ አደረጃጀቶችና አሰራሮች ዙርያ ዘርዘር ያሉ የመፍትሔ ኃሳቦች ተጠቁመዋል፡፡

በመቀጠል ውይይቱ ከሻይ እረፍት ሲመለስ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚና የቴሌቪዥን ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት አቶ አቤል አዳሙ የስፖርት አዘጋገብ በሚል ሰፋ ያለ ገለፃ ተደርጓል። አቶ አቤል ባቀረቡት ገለፃ ላይም ካላቸው የስራ ልምድና ንድፈ ሀሳባዊ ጉዳዮች ጋር በማያያዝ ለመዳሰስ ሞክረዋል፡፡

በመቀጠልም በአቶ ርስቱ ይርዳው፣ ኮሎኔል ዐወል እና አቶ ጌታቸው ባልቻ አወያይነት በቀጣይ የባለድርሻ አካላት ሚና ምን መምስል አለበት በሚል በተዘጋጀው ፅሁፍ ዙርያ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ብዙሀኑ ተሳታፊዎች በጋራ የተስማሙበት ጉዳይ በብሔራዊ እግርኳስ ፌደሬሽኑና በክለቦች መካከል ያለው ያለመተማመን ስሜት በስፋት በተሳታፊዎች የተነሳ ጉዳይ ሆኗል። በተጨማሪም ፌዴሬሽኑን በተመለከተ በህግ አተረጓገም ላይ ያለ መላላትና የእርምጃዎች ተመጣጣኝነት ዙሪያ በርካታ ኃሳቦች ተነስተዋል፡፡ በተጨማሪም በፌዴሬሽኑ ስር ተመዝግበው እውቅና ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ ክለቦች ስያሜንና አርማን እንዲቀይሩ የሚያደርግ አስገዳጅ ህጎችን ስለማውጣትና የስፖርታዊ ጨዋነትን የሚያበረታቱ ሽልማቶችን ማዘጋጀት የሚሉ ኃሳቦችም ተነስተዋል፡፡

በተነሱት ሀሳቦች ዙሪያ ምላሻቸው የሰጡት የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም ” በቅርቡ ስራው ለጀመረው አዲሱ የእግርኳስ ፌዴሬሽን ይህን መሠል ውይይቶችን በማካሄድ መጀመራችን በቀጣይ ለምናከናውናቸው ስራዎች ጥሩ ግብዓት ይሆኑናል ብለን እናስባለን፡፡ አሁን ላይ ያለው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በአንድ ጀምበር ምላሽ ሊያገኙ አይችሉም ፤ በቀጣይ በተለያዩ የክልል ክለቦች መካከል ወደ አንዱ ከተማ ሄደን ተዝዋዙረን አንጫወትም የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው እስካልቀረ ድረስ አሁን ባለው የውድድር ቅርፅ ይዞ ለመቀጠል ይቸገራል፤ በስፖርት ኮሚሽኑ ይሁንታ ካገኘ እንደ መፍትሔ ሀሳብ ያቀረብነው ወደ ቀደመው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የውድድር አካሄድ መመለሱ የሚያዋጣ አካሄድ መሆኑን ነው። ” ብለዋል።

በመጨረሻም የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው በጋራ ሁሉም ባለድርሻ አካል በአንድ ልብ በመስራት መጪውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ጉዞ ብሩህ እናድርግ የሚል መልእክታቸውን አሰተላልፈዋል፡፡ አይይዘው አሁን ያለው የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ቅርፅ ከመቀየር ይልቅ አሁን ባለው የውድድር ቅርጽ ህዝብ ለህዝብ ያለውን ግንኙነት በማጠናከር አብሮነታችንን ለማጎልበት መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡