ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ በመጨረሻ ደቂቃ አሳልፎ ሰጥቷል

በአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና 1-0 ሲመራ ቢቆይም በ89ኛው ደቂቃ እዮብ አለማየሁ ባስቆጠራት ግብ ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት ተገዷል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ጎንደር አቅንቶ ከፋሲል ከተማ ጋር 0-0 ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ በጉዳት ምክንያት ባልነበረው አህመድ ረሺድ ምትክ ተመስገን ካስትሮን በመስመር ተከላካይነት ሲጠቀሙ በተመሳሳይ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ቶማስ ስምረቱ እና ወጣቱን አጥቂ የኃላሸት ፍቃዱ በዛሬው ጨዋታ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት በአዲስ መልኩ በማምጣት ነበር የጀመሩት፡፡ በአንጻሩ ወላይታ ድቻዎች መቐለ 70 እንደርታን 1ለ0 ከረታው ቡድን ስብስብ ውስጥ በተከላካይ መስመር ላይ በዐወል አብደላ ምትክ ውብሽት አለማየሁን ብቻ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል፡፡


ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ወላይታ ድቻዎች ወደራሳቸው የሜዳ አጋማሽ በማፈግፈግ ጥቅጠቅ ብለው ለመከላከል ሲሞክሩ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሜዳው መሀከለኛ ክፍል ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢኖራቸውም እንደነበራቸው የበላይነት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ በጣም ተዳክመው ነበር፡፡ጨዋታው በተጀመረ ገና 11ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው አምበል ሙባረክ ሽኩር ባጋጠመው ጉዳት በአወል አብደላ ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል፡፡ በወላይታ ድቻ የሜዳ አጋማሽ በአመዛኙ አዘምብሎ በተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ 45 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ ቡናዎች የፈጠሯቸው የግብ ማግባት አጋጣሚዎች በሙሉ የተገኙት ከቆሙ ኳሶች ነበሩ፡፡ ከነዚህም መካከል በ14ኛው እና በ28ኛው ደቂቃዎች የኃላሸት እና አማኑኤል ከቋሙ ኳሶች ተሻምተው የተመለሱ ኳሶችን በመጠቀም በቀጥታ ወደ ግብ የላኳቸው ኳሶች በታሪክ ጌትነት ጥረት ግብ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ በነበሩበት በዚሁ የጨዋታ አጋማሽ በ40ኛው እንዲሁም 42ኛው ደቂቃ ላይ የኃላሸት ፍቃዱ እና ሚኪያስ መኮንን ከክፍት ጨዋታ ተጨማሪ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር። በአንጻሩ በመከላከል ላይ ተጠምደው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በሁለት አጋጣሚዎች ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። በተለይም በ19ኛው ደቂቃ እዮብ አለማየሁ አቀብሎት አንዱዓለም ንጉሴ ወደ ግብ የሞከራት እና ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ በላይ የወጣችበት ሙከራ የምትጠቀስ ነበረች፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንጻር ቀዝቀዝ ያለ ይዘት ነበረው። ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ ለመድረስ ተቸግረው በተስተዋሉበት በዚሁ አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተጫዋቾች ወደ ድቻ ሳጥን በተደጋጋሚ የሚልኳቸው ኳሶች በቀላሉ ሲበላሹ ተስተውሏል፡፡ ነገር ግን በ73ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ መኮንንን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ካሉሻ አልሀሰን በድቻው ግብጠባቂ ታሪክ ጌትነት ስህተት ታግዞ ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጠኑም ቢሆን ወደ ኃላ ለማፈግፈግ ማሰባቸው ለድቻዎች የተሻለ ሁኔታን ሊፈጥርላቸው ችሏል፡በተለይም ላይቤሪያዊዉ የኢትዮጵያ ቡና የመስመር አጥቂ ሰክላም ሾሌ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባበት ቅፅበት አንስቶ ቡድኑ በሚከላከልበት ወቅት በነበረው ደካማ ቦታ አያያዝ በተለይ በግራ መስመር በኩል በጣም ተጋላጭ ሆኖ ተስተውሏል፡፡


የጨዋታውን የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉት ድቻዎች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረትም ፍሬ አፍርቶ በ89ኛው ደቂቃ ላይ ኢስማኤል ዋቴንጋ የተፋውን ኳስ ተጠቅሞ እዮብ አለማየሁ ድቻን አቻ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ጨዋታውም ሁለቱ ቡድኖች ሳይሸናነፉ 1-1 በሆነ የአቻ ውጤት ያጠናቀቁት ሆኗል ፤ በዚህም ውጤት መሠረት ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን ወደ 8 ከፍ አድርጎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ድቻም ነጥቡን አምስት ማድረስ ችሏል፡፡


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ: LINK