ሪፖርት | አፄዎቹ መከላከያን አስተናግደው ነጥብ ተጋርተዋል

በስድስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአፄ ፋሲለደስ ስታድየም 09፡00 ላይ የጀምረው ጨዋታ ፋሲል ከነማን ከመከላከያ አገናኝቶ 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማዎች ባለፈው ሳምንት ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስን 1-0 ካሸነፈው ስብስብ በቤንጃሚን ኤዲ ኢዙ አዙካን እንዲሁም በያስር ሙገርዋ በዛብህ መለዮን በመተካት ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። በጦሩ በኩል ደግሞ አዲስ አበባ ላይ በወልዋሎ ዓ/ዩ 1-0 ከተሽነፉበት ስብስብ ፍሬው ሰለሞንን በዳዊት እስጢፋኖስ ፣ ዓለምነህ ግርማን በታፈሰ ሰርካ ለውጠው ጨዋታቸውን ጀምረዋል። 


ጨዋታው ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው እና ፋሲል ከነማን በተጫዋችነት እንዲሁም በስራ አስፈፃሚነት ላገለገለው አቶ ክንዱ ፍስሀ (ጉልጫ) የህሊና ፀሎት ሥነ ስርዓት በማከናወን ነበር የጀመረው።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች መሀል ሜዳ ላይ ትኩረት ያደረገ እንቅስቃሴ ነበር ሲያደርጉ የተስተዋለው። ነገር ግን ፋሲል ከነማዎች በቶሎ ግብ ማግኘት ችለዋል። በ10ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ ያሬድ ባየህ አክርሮ የመታውን ኳስ ሽመክት ጉግሣ ጨርፎ ወደ ግብነት ቀይሮት ነው ፋሲሎች መሪ የሆኑት። ሆኖም መሪነታቸው ከሁለት ደቂቃ አልዘለለም። ከቅጣት ምት የተሻማ ኳስ ምንይሉ ወንድሙ በጭንቅላት በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮ ጦሩን አቻ አድርጎታል። ጨዋታው በ1-1 ውጤት ቀጥሎም 19ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ በቀኝ መስመር ኳስ ይዞ በመግባት መጂብ ቃሲምን አልፎ በመሬት ያቀበለውን ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ ወደ ግብነት ቀይሮት እንግዳው ቡድን ሁለት ለአንድ መምራት ጀመረ።


በቀጣዮቹ ደቂቃዎች መከላከያዎች ወደ ኃላ ሸሸት ብለው ሲጫወቱ ፋሲል ከነማዎች በርካታ ዕድሎችን ፈጥረዋል። ከነዚህም ውስጥ 32ኛ ደቂቃ ላይ ከኢዙ አዙካ የተሻገረለትን ኳስ  ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ግብ አክርሮ ሞክሮ አቤል ማሞ ያወጣበት እንዲሁም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ኢላማውን ባይጠብቅም ራሱ ኢዙ አዙካ ከማዕዘን የተሻውን ኳስ በጭንቅላቱ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳል። በዚሁ አጋማሽ ሽመክት ጉግሳ እና ሙጂብ ቃሲምም እንዲሁ የአቤልን ጥረት ያልጠየቁ ሌሎች ሁለት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በዚህ መልኩ አጋማሹ እንግዳው ቡድን ሁለት ለአንድ እየመራ ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ኋላ አፈግፍገው ወጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ጥረት በሚያደርጉት ሰዓት 50ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ከተሻማ ኳስ ሰይድ ሁሴን ገጭቶ ያቀበለውን ሙጂብ ቃሲም ወደ ግብነት ቀይሮት አፄዎቹን አቻ መድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ፋሲሎች በማነቃቃት የተሻለ ተጭነው ተዳጋጋሚ የግብ ሙከራዎች ሲያደርጉ ታይተዋል። በኢዙ አዙካ እና በሽመክት ጉግሳ አማካይነት ከፈጠሩት ጫና በተጨማሪም በ67ኛው ደቂቃ አብዱረህማን ሙባረክ በቀኝ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ ወደግብ ሞክሮ ግብ ጠበቂው በቀላሉ አድኖበታል። 


በመከላከያ በኩል ዉጤት አስጠብቆ ለመውጣት አፈግፍገው ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በሙከራ ደረጃ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከመሀል ሜዳ ብቻውን ይዞ ገብቶ የግብ ጠባቂዉን መውጣት በመመልከት ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳተበት እጅግ ለቡድኑ የሚያስቆጭ ብቸኛ ሙከራ ነበር። በዚህ መልኩ ጨዋታው ሁለት ለሁለት በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አፄዎቹ  3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ መከላከያ በአንፃሩ 12ኛ ደረጃን ይዟል።