ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ከአስረኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር መካከል ሀዋሳ ከተማ ከመቐለ ከተማ የሚገናኙበትን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ሳምንት በተመሳሳይ የ3-1 ውጤት ተጋጣሚዎቻቸውን መርታት የቻሉት ሀዋሳ እና መቐለ ነገ እርስ በእስር ይፋለማሉ። መሪው ኢትዮጵያ ቡናን በአንድ ነጥብ እየተከተሉ ያሉት ሀዋሳዎች ቻምፒዮኖቹ አባ ጅፋሮችን  ከመመራት ተነስተው ካሸነፉበት ጨዋታ ማግስት እዛው ሜዳቸው ላይ ነው መቐለን የሚያስተናግዱት። ሀዋሳ በጅማው ድል ከሮዱዋ ደርቢ ሽንፈቱ በፍጥነት በማገገም ለዚህ ጨዋታ ደርሷል። መቐለ 70 እንደርታም ከሁለት ተከታታይ ግብ አልባ ጨዋታዎች በኋላ ነበር በዘጠነኛው ሳምንት ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ፤ ጨዋታው ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረበትም ሆኖ አልፏል። ሀዋሳ ከተማ ነገ ድል ከቀናው በኢትዮጵያ ቡና ውጤት ላይ ቢመሰረትም ቢያንስ ለአንድ ቀን ሊጉን በድጋሜ መምራት ሲችል መቐለም አምስት ደረጃዎችን የማሻሻል አጋጣሚ ሊፈጠርለት ይችላል።

በጉዳት ምክንያት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቀው የሀዋሳ ከተማው ዮሃንስ ሴጌቦ አሁንም ከክለቡ ጋር የሌለ ሲሆን ሌላኛው የመስመር ተከላካይ አይቮሪኮስታዊው ያኦ ኦሊቨር ግን ከስድስት ጨዋታዎች ቅጣት በኃላ ነገ ወደ ሜዳ ይመለሳል፡፡ በመቐለ በኩል ባሳለፈው ሳምንት ያልተሰለፉት አቼምፖንግ አሞስ እና አሸናፊ ሃፍቱ ከጉዳት ባለማገገማቸው ከቡድኑ ጋር ወደ ሀዋሳ አልተጓዙም። በተጨማሪም በሲዳማው ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ሳሙኤል ሳሊሶም ባለማገገሙ ይህ ጨዋታ የሚያልፈው ይሆናል።

ሀዋሳ ከተማ ነገም እንደተለመደው እስራኤል እሸቱን ማዕከል የሚያደርጉ ቀጥተኛ ኳሶችን እንደሚጠቀም ይጠበቃል። በመቐለ ከተማ በኩል ደግሞ የኳስ ቁጥጥርን መሰረት ያደተገ እና በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሚታገዝ የማጥቃት አቀራረብ ሊኖር እንደሚችል ይታሰባል። ሁለቱም ቡድኖች አምስት አማካዮችን እንደመጠቀማቸውም መሀል ሜዳ ላይ የሚኖረው ፉክክር ወሳኝነት ሊኖረው ቢችልም ሀዋሳዎች በቦታው ኳስ ከማንሸራሸር ይልቅ ወደ ፊት መጣልን የመምረጥ ዕድላቸው የሰፋ ነው።

በመሆኑም ከመቐለ የተከላካይ አማካዮች ጀርባ የሚጣሉ ኳሶች ለባለሜዳዎቹ ወሳኝነታቸው የጎላ ሲሆን ከፊት አጥቂው እስራኤል እሸቱ ባለፈ ግብ በማስቆጠር ሂደት ውስጥ እየተሳተፉ የሚገኙት የቡድኑ አማካዮች በቦታው የሚኖራቸው ሚና ከፍ ያለ ነው። በሌላ ወገን እንግዶቹ መቐለዎች የማጥቃት ባህሪ በተላበሱ አማካዮቻቸው ወደ ውስጥ አጥብበው ለማጥቃት የሚሞክሩበት ሂደት እንደሚኖር ይጠበቃል። ይህ አካሄድ በቡድኑ ሲተገበር በብዛት የመስመር ተከላካዮች ተሳትፎ ሲጨመርበት የሚታይ ባለመሆኑ ከአጥቂው ጀርባ የሚሰለፉት ሦስቱ አማካዮች ከሀዋሳ ተከላካዬች ፊት ከሚኖረው የሁለትዮሽ ጥምረት ጋር መፋለም ይጠበቅባቸዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– መቐለ ወደ ሊጉ በመጣበት የአምናው የውድድር ዓመት ሁለቱ ክለቦች ሀዋሳ ላይ ተገናኝተው ጨዋታቸው ያለግብ ሲጠናቀቅ በሁለተኛው ዙር መቐለ 1-0 አሸንፏል።

– ሀዋሳ ከተማ እስካሁን ሀዋሳ ላይ ካደረጋቸውን ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ አምስቱን በድል ሲያጠናቅቅ 16 ግቦችን ከመረብ ማገናኘት ችሏል።

– በሦስት ጨዋታዎች ከትግራይ ስታድየም ውጪ ያደረገው መቐለ 70 እንደርታ አንድ ነጥብ እና አንድ ግብ ብቻ ይዞ ነበር የተመለሰው።

ዳኛ

– እስካሁን ሁለት ጨዋታዎችን መርቶ አስራ ሁለት የቢጫ ካርዶችን የመዘዘው ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ይህንን ጨዋታ ይዳኛል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ ( 4-2-3-1) 

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሃንስ

አዳነ ግርማ – መሣይ ጳውሎስ

ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ታፈሰ ሰለሞን – ኄኖክ ድልቢ

እስራኤል እሸቱ

መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)

ፍሊፔ ኦቮኖ

ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ

ያሬድ ከበደ – ሐይደር ሸረፋ – ዮናስ ገረመው

አማኑኤል ገብረሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *