ሪፖርት | መቐለ ሀዋሳን በሜዳው ድል አድርጎታል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ወደ ሀዋሳ የተጓዘው መቐለ70 እንደርታ ሀዋሳ ከተማን በአማኑኤል ገብረሚካኤል ብቸኛ ግብ ረቷል፡፡

ሀዋሳ ከተማ በዘጠነኛው ሳምንት ከተጠቀመበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን በመቐለ በኩልም የተደረገው አንድ ቅያሪ ብቻ ነው። በዚህም በሲዳማው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ሳሙኤል ሳሊሶ በቢያድግልኝ ኤልያስ ተተክቷል፡፡

የመጀመሪያዎቹን 10 ደቂቃዎች መቐለዎች አጥቅተው ለመጫወት ወደ ሜዳ የገቡ ቢመስልም ቀስ በቀስ በሀዋሳ ከተማ ብልጫ ተወስዶባቸዋል፡፡ ሀዋሳዎች በቀኝ እና ግራ መስመር ተመላላሽነት ከተሰለፉት ደስታ ዮሀንስ እና ዳንኤል ደርቤ እግር ስር ከሚነሱ ኳሶች ወደ እስራኤል እሸቱ በቀጥታ ማድረስን ያለመ አጨዋወት ተከትለዋል፡፡ ይህንን አጨዋወት በይበልጥ ይጠቀሙ እንጂ አማካዩ ታፈሰ ሰለሞን ወደ አዳነ ግርማ ተጠግቶ ቅብብሎችን በመከወን ወደ መስመር በማድረሱም አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ በዚህም 5ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ የመቐለ የግብ ክልል በኩል ዳንኤል ሲያሻግር እስራኤል እሸቱ በክፍት አጋጣሚ ያገኛትን ኳስ በቀላሉ አምክኗታል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ በተመሳሳይ ደስታ ከግራ አቅጣጫ ያሻማትን ኳስ አምበሉ አዳነ ግርማ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ወጥታበታለች፡፡

መቐለ 70 እንደርታዎች በሂደት የሀዋሳዎችን የኮሪደር እንቅስቃሴን መከላከሉ ላይ የተሳካላቸው ቢሆንም በማጥቃት ለመጫወት ያደረጉት ጥረት ግን እምብዛም አልነበረም፡፡ አማካይ ክፍል ላይ ብልጫ የተወሰደባቸው መሆኑና ከተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በጣም በመራቃቸው ምክንያት በቀጥታ ለአጥቂዎቹ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ያሬድ ከበደ በሚላኩ ኳሶች ላይ ለመመርኮዝም ተገደዋል፡፡ በተለይም 18ኛው ደቂቃ ላይ የያሬድ እና አማኑኤል ጥምረት አማኑኤልን ከሶሆሆ ጋር ቢያገናኘውም ግብ ጠባቂው ቀድሞ አውጥቶበታል፡፡ ጨዋታው በማዕዘን ምት ሲቀጥልም ሀይደር ሸረፋ አሻምቶ ተከላካዩ ቢያድግልኝ ኤልያስ በግንባሩ ቢገጭም ሙከራው ግቡን ቋሚ ታኮ ወጥቷል፡፡ ከዚህ ውጪ ቡድኑ ጠንካራ ሙከራ ያደረገው 41ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን አንተነህ ገብረክርስቶስ ከሄኖክ ድልቢ የነጠቀውን ኳስ ለሀይደር ሰጥቶት ሀይደር ከሳጥን ውጪ ቢሞክርም ኢላማውን አልጠበቀም ነበር፡፡

በተመሳሳይ አጨዋወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት ሀዋሳዎች በመጠኑም ቢሆን በመጨረሻወቹ 10 ደቂቃዎች ተሳክቶላቸው ነበር ፡፡ 33ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሞክሮ አሚኑ ነስሩ ተደርቦ ያወጣበት ሙከራ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ ቡድኑ ከመስመር ከሚያሻግራቸው ኳሶችም ይበልጥ አደገኛ ሆኖ መታየቱንም የቀጠለ ሲሆን በሶስት የግንባር ኳሶች አዳነ ግርማ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ ከዚህ ውጭ 45ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በተከፈተ መልሶ ማጥቃት ከዳንኤል ደርቤ ያገኛትን ዕድል እስራኤል እሸቱ ሳይጠቀምባት የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ ዮናስ ገረመውን በቢያድግልኝ ኤልያስ በመቀየር የተከላካይ ክፍላቸውን ወደ አራት ያሳደጉት መቐለዎች ይበልጥ የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት ሂደት ለመግታት የተሻለ ቅርፅን ይዘው ገብተዋል፡፡ ሆኖም ሀዋሳዎች በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች በኄኖክ ድልቢ ከሁለት የቆሙ ኳሶች ሙከራዎች ሲያደርጉ አንደኛዋ ወደ ውጪ ስትወጣ ሁለተኛዋ ደግሞ የግቡ ቋሚ መልሷታል፡፡ በአንፃሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚን ይጠብቁ የነበሩት መቐለዎች በሚፈልጉት መንገድ ለብቸኛው አጥቂያቸው ያሬድ ከበደ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተስኗቸው ቆይተዋል ፡፡

የማጥቃት ኃይላቸውን ይበልጥ ለማጎልበት ያሰቡት ሀይቆቹ 60ኛው ደቂቃ ላይ ደስታን በብሩክ በየነ ከቀየሩ በኃላ ግን የግራ መስመር የተከላካይ ክፍላቸው ለተጋጣሚያቸው የተመቸ ሆኗል፡፡ በዚህም አማኑኤል ከቀኝ መስመር በመነሳት በተደጋጋሚ የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል በማስጨነቅ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ልዩነት መፍጠር ችሏል፡፡ 67ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ከያሬድ ተቀብሎ በመግባት ሊመታ ሲል አዲስዓለም ተስፋዬ ያስጣለው ሲሆን 75ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ አማኑኤል ለያሬድ የፈጠረለትን ዕድል ሶሆሆ ሜንሳህ እንደምንም ይዞበታል፡፡ ነገር ግን የመቐለወች ተደጋጋሚ ጥረት 81ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል፡፡ ከራሳቸው የግብ ክልል አንተነህ ገብረክርስቶስ የላከለትን ኳስ አማኑኤል በዛው ቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት የጨዋታውን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡

ባለሜዳዎቹ ሀዋሳዎች ምንም እንኳን ለመልሶ ማጥቃት ቢጋለጡም ግብ ከማስተናገዳቸው በፊት ጀምሮ ከማጥቃት አልቦዘኑም፡፡ 78ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ቸርነት አውሽ ያሻማውን ኳስ እስራኤል እሸቱ በግንባሩ ገጭቶ በላይኛው የግቡ ብረት ለጥቂት የወጣበት ሙከራም ተጠቃሽ ነው፡፡ ከአማኑኤል ጎል በኃላም መቐለዎች ወደ ኃላ ባያፈገፍጉም ሀዋሳዎች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ሙሉ ኃይላቸውን ተጠቅመው ኳሶችን ወደ ፊት ለመጣል ይሞክሩ ነበር፡፡ በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን ያመከነው እስራኤል እሸቱን በገብረመስቀል ዱባለ በመተካትም ከጥልቅ አማካይ ስፍራ ላይ ይነሳ በነበረው ታፈሰ ሰለሞን ላይ ተመስርተው ያደረጓቸው ጥረቶች የታዩ ቢሆንም ወደ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሳይለውጧቸው ጨዋታው በመቐለ 70 እንደርታ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *