ከፍተኛ ሊግ ሐ | ሀድያ ሆሳዕና በአሸናፊነት ጉዞ ሲቀጥል አርባምንጭ አሸንፏል

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ ሰባተኛ ሳምንት አምስት  ጨዋታዎች እሁድ ሲከናወኑ ሀዲያ ሆሳዕና፣ አርባምንጭ ከተማ እና ነቀምት ከተማ ተጋጣሚያዎቻቸውን አሸንፈዋል። 

ሀዲያ ሆሳዕና 3-1 ካፋ ቡና

(በአምሀ ተስፋዬ)

ሆሳዕና ላይ ካፋ ቡናን ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና 3-1 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል። ጨዋታውን በማጥቃት የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የከፋ ቡናን የግብ ክልል መፈተሽ የጀመሩት ገና በግዜ ነበር። በአንደኛው ደቂቃ ኢዩኤል ሳሙኤል ባደረገው የግብ ሙከራ አድርገዋል። በመልሶ ማጥቃት መጫወት ምርጫቸው ያደረጉት ከፋ ቡናዎች በ11ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ የግብ ሙከራቸውን ከርቀት የተገኘ ቅጣት ምት አብነት አባቴ ሞክሮ በግቡ አናት ወጥታበታለች። በ13ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያ ሆሳዕና ተከላካይ አዩብ በቃታ እና የግብ ጠባቂው ስህተት እድል ያገኘው ኦኒ ኦጅሉ ወደ ግብነት ለውጦ ካፋ ቡናን ቀዳሚ አድርጓል። 

ከግቡ መቆጠር ባኋላ ወደ ኋላ አፈግፍገው ግብ እንዳይቆጠርባቸው የጣሩት ካፋ ቡናዎች ጥረታቸው መግፋት የቻለው እስከ 31ኛው ደቂቃ ድረስ ብቻ ነበር። በ31ኛው ደቂቃ ላይ ከቀድሞ የሀላባ ተጫዋች ስንታየው ያገኘውን ኤቶኤል ሳሙኤል የአቻነት ጎሉን ለሀዲያ ሆሳዕና ማስቆጠር ችሏል። ከግቡ መቆጠር ባኋላ ወደፊት ጫን ብለው ለመጫወት ፍላጉት ያሳዩት ከፋዋች ወዲያው ወደ መልሱ ማጥቃት አጨዋወታቸው ተመልሰዋል። ሆኖም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጫና ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት ሆሳዕናዎች በተለይም ኤሪክ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገኛኝቶ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ የቀኝ አግዳሚ የወጣባት ኤቶኤል ሳሙኤል አራት ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ግብ መትቶ ኳፀግብ ጠባቂው ያዳነበት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ። በግራ መስመር ፍራኦል መንግስቱ ያሻማውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ኤሪክ ሙራንዳ በግንባሩ በመግጨት የሆሳዕናን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። በ79ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተቀይሮ የገባው ዳግም በቀለ ከከፋ ግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በግሩም አጨራረስ በማሳረፍ የሀዲያ ሆሳዕናን የግብ ልዩነት ከፍ ማድረግ ችለዋል። ጨዋታውም በሆሳዕና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ 1-0 ሻሸመኔ ከተማ

(በፋሪስ ንጉሴ)

አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ከሻሸመኔ ያደረጉት ጨዋታ እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ግብ ሳይቆጠር ቢቆይም የማታ ማታ ባለሜዳው አርባምንጭ ማሸነፍ ችሏል። የማጥቃት ባህሪ የታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ጥሩ የኳስ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩትም የሁለቱም ክለቦች የተከላካይ ክፍሎቻቸው ጠንክረው በመቅረባቸው የጎል ሙከራ ለማድረግ ግማሽ ሰዓት መጠበቅ የግድ ነበር። በ28፣ በ32 እና በ35ኛው ደቂቃ ላይ በአለልኝ አዘነ እና ብርሃኑ አዳሙ በተደረጉት ሙከራዎች አርባምንጮች የመጀመርያውን አጋማሽ ሲያጠናቅቁ እንግዳው ቡድን ደግሞ ሰዓት ሲያባክንና የተደራጀ የመከላከል ታክቲኩን ተጠቅሞ ግብ ሳይቆጥርበት ለመውጣት ያደረገውን ትግል በመጀመርያው አጋማሽ አሳክቶት ወጥቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው አጋማሽ ብዙም ያልተሻለ ሲሆን አርባምንጮች ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ብዙም አመርቂ ያልሆነ ቅብብል እና ቶሎ ቶሎ የሚበላሹ ረጃጅም ቅብብሎች ጨዋታውን ሲያቀዘቅዙት ሻሸመኔዎች ደግሞ እጅግ የተደራጀ የመከላከል ታክቲካቸውን ሳይቸገሩ ሲተገብሩ ውለዋል። በ56፣ በ61 እና በ86ኛው ደቂቃ ላይ በአሸናፊ ኤሊያስ፣ በመስቀሉ ሌታቦ እና በቴዲ ታደሰ ከረጅም ርቀት እና በግንባር የተገጩ ኳሶች በሻሸመኔ ግብ ጠባቂ በቀላሉ ተይዞባቸዋል። ከነዚህ ሙከራዎች በኋላ በአለልኝ አዘነ ከርቀት የተመታ ኳስ በሻሻመኔ ተጫዋች በእጅ ተነክቷል በሚል ጭቅጭቅ አሰንስቶ ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተቋርጦ እንደገና ጨዋታው ተጀምሯል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት የሻሸመኔ ተከላካዮች ወደ ጎላቸው ተጠግተው በመከላከላቸው ኳሶች በተደጋጋሚ ወደ ግብ ክልል ይደርሱ ነበር። በስተመጨረሻም ቴዲ ታደሰ ወደ ጎል የመታው ኳስ የሻሸመኔ ተከላካይ ተደርቦ የማዕዘን ምት ለአርባምንጮች ይሰጣል። ይህ የመጨረሻ ዕድላቸው በመሆኑ አርባምንጮች ግብ ጠባቂው ሲቀር ሁሉም በሻሸመኔ የግብ ክልል ውስጥ ተገኝተዋል። ቴዲ ታደሰ ያሻማውን የማዕዘን ምትም በረከት ወ/ዮሐንስ በግንባሩ ገጭቶ ለአርባምንጭ ከተማዎች ሦስት ነጥብ የምታስገኘውን ወሳኝ ግብ አስቆጥራል። ጨዋታውም በአርባምንጭ ከተማ 1ለ0 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቤ ከ ቤንች ማጂ ቡና ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በ16ኛው ደቂቃ እንግዳው ቤንች ማጂ ከማል አቶም ባስቆጠረው ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችልም ከእረፍት መልስ ወራቤዎች የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ጨዋታ ላይ ከስልጤ ወራቤ በ34ኛው ደቂቃ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ወጥቷል።

ሺንሺቾ ላይ ሺንሺቾ ከ ነገሌ ቦረና 1-1 አቻ ሲለያዩ ቢሾፍቶ አውቶሞቲቭ በሜዳው በነቀምት 1-0 ሽንፋት አጋጥሞታል። ጅማ ላይ በጅማ አባ ቡና እና ቡታጅራ መካከል ሊደረግ የነበረው ጨዋታ ደግሞ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል።

Leave a Reply