ፋሲል ከነማ በወዳጅነት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ላይ አምስት ግቦችን አስቆጥሮ አሸንፏል

ሁለት አላማን ሰንቆ የተከናወነው የባህር ዳር ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ ዛሬ 10 ሰዓት በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ሲደረግ ዐፄዎቹ 5-0 አሸንፈዋል።

የሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ከትላንት በስትያ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲጓዝ ድንገተኛ አደጋ አጋጥሞት የሁሉንም ተጓዦች ህይወት ለቀጠፈው ክስተት የህሊና ፀሎት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ክለቦች ለሁለተኛው ዙር ዘግጅት እና የወዳጅነት ጨዋታዎች እያደረጉ ሲሆን ዛሬ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም በጎ አላማን የያዘ ጨዋታ ተከናውኗል። ተጨዋቾቻቸውን ወደ ጨዋታ ሪትም ከማስገባት ባለፈ በጎ አላማን ሰንቀው ወደ ሜዳ የገቡት ሁለቱ ቡድኖች በተለይ በአደጋ እና በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች ማቋቋሚያ የሚሆን ገቢ ለማግኘት ነበር ጨዋታቸውን ያከናወኑት።

ሁለቱም ክለቦች የፊታችን እሁድ በሜዳቸው ቅዱስ ጊዮርጊስን (ባህር ዳር ከተማ) እና ሲዳማ ቡናን (ፋሲል ከነማ) ከማስተናገዳቸው በፊት አቋማቸውን ለመፈተሽ ይጠቅማቸዋል ተብሎ በታሰበለት ጨዋታ ፋሲል ከተማዎች ብልጫ ወስደው ሲንቀሳቀሱ በርካታ ግቦችንም በባለሜዳዎቹ ላይ አስቆጥረው አሸንፈዋል። ፋሲሎች በ8፣ 37 እና 41ኛው ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም ባስቆጠረላቸው ሐት-ትሪክ እንዲሁም በ53 እና 90ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ዓለሙ እና ፋሲል አስማማው ባስቆጠሯቸው አንድ አንድ ግቦች ታግዘው ነው ባህር ዳር ከተማን በሰፊ የግብ ልዩነት ያሸነፉት። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ የተስፋ ቡድን ተጨዋቾችን በማስገባት ለተስፈኛ ታዳጊዎች እድል በመስጠት ተጫውተዋል።

ጨዋታውን ለመታደም የገቡ የባህር ዳር ከተማ አንዳንድ ደጋፊዎች አዳዲስ ተጨዋቾችን ክለቡ እንዲያስፈርምላቸው እና በሁለተኛው ዙር ተጠናክረው እንዲቀርቡ እንዲሁም ግልጋሎት የማይሰጡ ተጨዋቾች ከክለቡ እንዲሰናበቱ በስታዲየሙ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ተሰምቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *