“መቐለን ቻምፒዮን ማድረግ፤ በግሌም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ መሆን እፈልጋለው” አማኑኤል ገ/ሚካኤል

በኢትዮጵያ እግርኳስ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ክስተት ሆነው ብቅ ካሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ፍጥነቱ ፣ ያገኛቸውን የጎል አጋጣሚዎች የመጠቀም አቅሙ ልዩ ነው። 2009 ላይ በከፍተኛ ሊግ በነበረው ቆይታ 17 ጎሎች በማስቆጠር ዓመቱን በኮከብ ተጫዋችነት አጠናቋል። በሦስት ዓመታት የመቐለ 70 እንድርታ ቆይታው ዘንድሮ ለቡድኑ ተከታታይ ድል እና የዋንጫ ተፎካካሪነት ትልቁን ድርሻ እየተወጣም የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ዘንድም ዕድል እየተሰጠው ይገኛል። መተማ ተወልዶ ያደገው እና ከልጅነቱ ጀምሮ በኳስ ፍቅር የተለከፈው አማኑኤል ገብረሚካኤል ስለ ወቅታዊ አቋሙ እና የመቐለ 70 እንድርታ አስደናቂ ግስጋሴን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን በሚገኘበት ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ያለፉትን ሦስት ዓመታት ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር እያደረግኽ ያለውን ቆይታ እንዴት ይገለፃል ?

ሦስት ዓመታትን ከመቐለ ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው። በከፍተኛ ሊግ በነበረኝ ቆይታ እንደሚታወቀው ከብዙ ውጣ ውረድ እና ትግል በኋላ ድሬዳዋ ላይ በተደረገው የመጨረሻ ጨዋታ እኔ ባስቆጠርኩት ጎል መቐለን ወደ ፕሪምየር ሊግ የማስገባት ዕቅዳችንን አሳክተናል። ከዚህ ባለፈም በግሌ ኮከብ ተጫዋች ሆኜ ተመርጫለው። ያ ዓመት ለእኔ ልዩ ነበር። ወደ ፕሪምየር ሊግ ገብተን ደግሞ እኔም ሆንኩ ክለቤ ለሊጉ አዲስ ስለነበርን ዋናው ዕቅዳችን ቡድኑን በሊጉ ማቆየት በመሆኑ ይህን አሳክተናል። እኔም ለመጀመርያ ጊዜ በሊጉ እንደመጫወቴ መልካም የሚባል ጊዜ ነበረኝ። ዘንድሮ የሊጉ መሪ መሆን ችለናል ፤ ጥሩ ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። ዋንጫውንም ለማንሳት በቀሩት ጨዋታዎች ጥሩ ነገር እንሰራለን። በአጠቃላይ በመቐለ ያለኝ ቆይታ አስደሳች ነው።

በሦስት ዓመታት ቆይታህ ከተለያዩ የአጥቂ ባህሪ ካላቸው የውጪ ሀገር ዜግነት ካላቸው እና ከሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ጋር ተጣምረሀል። የትኛው ተጫዋች ለአንተ ተመችቶሀል?

አዎ ከተለያዩ ተጫዋቾች ጋር ተጫውቻለው። በሦስቱም ዓመታት አብሮኝ እየተጫወተ ከሚገኘው ያሬድ ከበደ ጋር ያለኝን ጥምረት ነው ለእኔ ጥሩ ጥምረት የምለው። አምና እንደ አጋጣሚ ሆኖ ብዙ አብረን ተጣምረን አልተጫወትንም። ዘንድሮ ግን አብረን በመጫወት ጥሩ እየተጓዝን ነው የምንገኘው። በብሔራዊ ቡድንም አብረን ለመጠራት በቅተናል። በአጠቃላይ ለእኔ ያሬድ አጠገቤ ሆኖ ሲጫወት ይመቸኛል።

መቐለ 70 እንድርታ በዘንድሮ ዓመት ለዋንጫ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው ቡድኖች አንዱ ነው። በተከታታይ ጨዋታም እያሸነፋቹ ነው። ይህን ጥንካሬያችሁን እንዴት ትገልፀዋለህ?

ተከታታይ ጨዋታ በማሸነፋችን በጣም ደስተኞች ነን። አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም ውጤታችን ተበላሽቶብን ነበር። ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ጋር ቁጭ ብለን ተነጋግረን ችግራችንን በመፍታት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግበናል። ለዚህም አሰልጣኛችን የሚሰጠንን ተቀብለን ጠንክረን ስለምንሰራ እና ሁሌም በሜዳችንም ከሜዳም ውጪ ለማሸነፍ መጫወታችን ተከታታይ ድል ለማስመዝገባችን ጠቅሞናል። ቡድናችን ውስጥ ህብረት እና አንድነት መኖሩም እንዲሁ የጠቀመን ይመስለኛል።

የቀድሞው የፌስቡክ ገፃችን በኛ ቁጥጥር ስር የማይገኝ በመሆኑ አዲሱ ገፃችንን ሊንኩን በመከተል ላይ ያድርጉ – facebook.com/SoccerEthiopiaበሜዳ ላይ በጣም ፈጣን እና እንቅስቃሴህም ለተከላካዮች ፈታኝ ነው። ይህ ፍጥነትህ ከየት የመጣ ነው?

(እየሳቀ) እኔንጃ ከየት አገኘዋለው ብለህ ነው። በተፈጥሮ ፈጣሪ የሰጠኝ ስጦታ ነው። በልምምድ ወቅት ለፍጥነት ብዬ የምሰራው የተለየ ነገር የለም። አሰልጣኜ የሚሰጠኝን ልምምድ በተገቢው ሁኔታ እሰራለው እንጂ እንዲህ ነው ብዬ የምገልፀው ነገር የለኝም ፤ በተፈጥሮ ያገኘሁት ነው።

በተጋጣሚዎች ከሚሰጥህ ትኩረት አንፃር ሜዳ ውስጥ ለኃይል አጨዋወት ትጋለጣለህ ሆኖም ብትጎዳም በድጋሜ ተመልሰህ ተከላካዮችን ስታስቸግር ትታያለህ። በዚህ ተክለሰውነት ይህን ጥንካሬ እንዴት አመጣኸው ?

(ፈገግ እያለ) ያው አውቃለው ወደ ሜዳ ስገባ ይህ ሊያጋጥመኝ እንደሚችል ፤ ቀድሜ ተዘጋጅቼ ነው የምገባው። ራሴን ከጉዳት ለመጠበቅ እዘጋጃለው። ያም ቢሆን የተለያዩ ጉዳቶችን አስተናግዳለው። ቅድም እንዳልኩህ የተለየ የምሰራው የጥንካሬ ስራ የለም። ኳስ ተጫዋች ስትሆን ዱላዎች ያጋጥሙሀል ፤ እነዚህን ችግሮች ተቋቁመህ ማለፍ ይገባሀል። እነዚህን አልፌ ነው እየተጫወትኩ ያለሁት።

በወጥነት ራስህን ከጉዳት ጠብቀህ በብዙ ጨዋታዎች በመጫወት በተከታታይ ጎሎችን እያስቆጠርክ ትገኛለህ። ይሄን እንዴት ትገልፀዋለህ ?

አዎ። ቡድናችን አጥቅቶ የሚጫወት ነው። ስለዚህ በተደጋጋሚ ወደ ጎል የመድረሳችን ነገር ጥሩ ነው። ለእኔም ያላቸው ነገር አሪፍ ነው። ስብስባችን እንደምታዩት ከአምናው በተሻለ ጠንካራ ነው። አሰልጣኛችንም የሚሰጠን ስልጠና በጣም ተመችቶኛል። ይህ ደግሞ እኔ በተሻለ ጎል እንዳስቆጥር አድርጎኛል። በተለይ በዘንድሮ ዓመት ለእኔ በጣም ነው ቀሎኝ እየተጫወትኩ ያለሁት።

ከምንይሉ ወንድሙ ጋር በዕኩል 11 ጎሎች እየተፎካከራችሁ የመጀመርያውን ዙር አጋምሳችኋል። በሁለተኛው ዙር ምን እንጠብቅ ?

መቐለ የውድድሩ አሸናፊ እንዲሆን በማድረግ እኔም በግሌ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኜ ማጠናቀቅ እፈልጋለው። ለዚህም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ጠንክሬ እሰራለው።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዋናውም በኦሊምፒክ ቡድኑም እየተጠራህ ነው። ስለ ብሔራዊ ቡድን አጠቃላይ ጉዞህ ንገረኝ እስኪ ?

በብሔራዊ ቡድን ያለኝ ነገር ለእኔ በጣም አሪፍ ነው። እንደመጀመርያ በሊጉ ብዙ ላልቆየ ተጫዋች መልካም የሚባል ነው። ብዙ ልምድ እያገኘሁበት ነው። መጀመርያ ወደ ብሔራዊ ቡድን ስመጣ ልምምድ እሰራለው ከዛ ከጨዋታ ውጪ እሆን ነበር። አሁን ደግሞ ተቀይሬ መግባት እየጀመርኩ ነው። በቀጣይ ደግሞ የተሻለ ነገር ይመጣል ብዬ አስባለው። በብሔራዊ ቡድን ቆይቼ ወደ ክለቤ ስሄድ በራስ መተማመኔ እየጨመረ እና ልምድ እያገኘው ጥሩ መሻሻሎችን እያሳየሁ ነው።

የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች እና የሜዳ ድባቡን እንዴት ትገልፀዋለህ ?

የመቐለ ደጋፊን እንዴት እንደምገልፀው አላውቅም ፤ ከቃላት በላይ ነው። ለእኔ ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው። ስለ እነርሱ በደንብ የምናውቀው በውስጡ ያለን ተጫዋቾች ነን ። ሦስት ዓመቴ ነው ፤ ደጋፊዎቹ ልዩ ናቸው። የሚገርም ደስ የሚል ድባብ ነው ያለው። እኔ ከምለው በላይ ሁሉም ያውቀዋል። በዚህ አጋጣሚ ደጋፊዎቻችንን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለው።

የወደፊት ዕቅድህስ ምንድን ነው?

በእግርኳስ ህይወቴ ከዚህ የተሻለ ነገር መስራት እፈልጋለው። አሁን የማስበው ከመቐለ ጋር የዘንድሮ የሊጉን ዋንጫን በማንሳት ታሪክ መስራትን ነው። በቀጣይ ከዚህ በተሻለ መጫወት እፈልጋለው።

ዘንድሮ ከመቐለ ጋር ያለው ኮንትራትህ ያበቃል። ቀጣይ ውሳኔህ ምድነው ?

እሱን አሁን ላይ ሆኜ መናገር አልችልም። ምክንያቱም ጥሩ ነገር አይሆንም። ለእኔም ከአሁን ጀምሮ መወሰን ጥሩ አይደለም። በራሴ ላይ ጫና መፍጠር አልፈልግም።

ከኢትዮጵያ ተጫዋቾች ማንን ታደቃለህ ?

ጌታነህ ከበደን አደንቃለው እርሱ ለጎል ያለውን ነገር እና አጨራረሱን እወድለታለው። እንደዚሁም የሳላዲን ሰዒድም በጣም አድናቂ ነኝ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

error: