ጅማ አባቡና አሰልጣኝ ሲቀጥር ሦስት ተጫዋቾች አስፈርሟል

በከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ እየተወዳደረ የሚገኘው ጅማ አባ ቡና የቀድሞ አሰልጣኙን መልሶ ሲቀጥር ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

አሰልጣኝ አንተነህ አበራ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ቡድኑ ተቀላቅለዋል። በባለፈው ዓመት የአሰልጣኝ ግርማ ሐብተዮሐንስን ስንብት ተከትሎ አባቡናን በመረከብ በከፍተኛ ሊጉ እስከ መለያ ጨዋታው ማድረስ ቢችሉም በአወዛጋቢ ሁኔታ ከቡድኑ ከተለያዩ በኋላ በድጋሚ የአሰልጣኝ መኮንን ማሞ ስንብት ማግስት ወደ ጅማ አባቡና ተመልሰዋል።

አሰልጣኝ አንተነህ በዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ በምድብ ሐ በ13 ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃን በመያዝ የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቀው ጅማ አባ ቡናን ወደ ተፎካካሪነት የመመለስ ኃላፊነት ተጥሎባቸው።

ጅማ አባ ቡና ከአሰልጣኝ በተጨማሪ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። ከደደቢት የለቀቀው የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ምስጋናው መኮንን በካርሎስ ዳምጠው ላይ ጥገኛ የሆነው የአጥቂ ክፍሉን እንደሚያጠናክር ሲጠበቅ በአማካይ ስፍራ ላይ ታከለ ታንቶን ከወልቂጤ ከተማ፣ ጅላሉ ከማልን ከአውስኮድ ማስፈረም ችለዋል። ከታዳጊ ቡድኑ ደግሞ አይመል ሸምሰዲን ኤና ተመስገን ድንቁን ወደ ዋናው ቡድን አሳድገዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *