የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 1-2 ደደቢት

ከ19ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ውስጥ አዲስ አበባ ላይ ደደቢት መከላከያን 2-1 ከረታበት ጨዋታ በኋላ በቡድኖቹ አሰልጣኞች በኩል ተከታዮቹ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

” የሚፈለገውን ሦስት ነጥብ አሳክተናል” ዳንኤል ፀሀዬ – ደደቢት

ስለጨዋታው

“እንደአጋጣሚ ሆኖ በጭቃ ያደረግነው ሦስተኛ ጨዋታ ነው። ከሁለት ቀን ብቻ እረፍት በኋላ ያደረግነውም ጨዋታ ነው። እንደምንፈልገው ኳስ ይዘን በመጨዋቱ ጥሩ ባንሆንም በሽንፈት ከመቆየታችንም አንፃር የሚፈለገውን ሦስት ነጥብ አሳክተናል። ውድድሩ ገና 11 ጨዋታ ይቀረዋል ፤ 33 ነጥብ ማለት ነው። የተወሰነውን እንኳን ብናሸንፍ ወደ ላይ መምጣት እንችላለን። ነጥቡ እየጠበበ ነው። አሁን ደግሞ በተከታታይ አራት ጨዋታዎችን ሜዳችን ላይ ስለምናደርግ የተሻለ ዕድል ይኖረናል።”

በቡድኑ ውስጥ የተለወጡ ነገሮች…

” ቡድናችን ውስጥ ትልቅ መነሳሳት አለ። ተጨዋቾቹ ሜዳ ላይ እንደሚያደርጉት ሁሉ በልምምድ ወቅትም ጠንክረው እየሰሩ ነው። ቡድኑን ማትረፍ እንደሚችሉም እምነቱ አላቸው። የማጥቃት ኃይላችን እንደምንፈልገው ባይሆንም ለውጥ አለው። የመከላከል አቅማችንም በወጣቶች የተሰራ ሳለሆነ ድክመቶች አሉበት ለማስተካከልም እየሰራን ነው። ”

ስለመድሀኔ ብርሀኔ የአጥቂነት ሚና….

” ተጫዋቹ እንደየጨዋታው በተለያዩ ቦታዎች የመጫወት አቅም አለው። በተከታታይም ግቦችን አስቆጥሯል። ከዚህ በኋላም በአጥቂነት ብንጠቀመው እና የሚቀሩት ማስተካከል የሚገባውን ነገሮች ካስተካከለ ባለው ተሰጥዖ በድኑን ይጠቅማል ብዬ አስባለው። ”

” እንደቡድን ሁሉም ተጫዋቾቼ የሚቻላቸውን ያህል ነው ያደረጉት ” አሰልጣኝ ስዩም ከበደ – መከላከያ

ስለጨዋታው

” ዛሬ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ዘጠና ደቂቃውን ሙሉ ጥሩ ተጫውተናል። ትልቁ ችግራችን የነበረው ያገኘናቸውን ዕድሎች አለመጠቀማችን ነው። እንደቡድን ሁሉም ተጫዋቾቼ የሚቻላቸውን ያህል ነው ያደረጉት። በስህተት የተቆጠሩብን ግቦች ተጋጣሚያችንን እያነሳሳው የሄደ ይመስለኛል። እንደቡድን ግን መደረግ ያለበት ነገር ሁሉ ተደርጓል። ተጫዋቾቼ ያደረጉት ጥረት በሙሉ ከጠበኩት በላይ ነው። ድሬዳዋ ላይ በጣም ጥሩ ነበርን የዛሬው ደግሞ ከዛን የተሻለ ነበር። ”

የቡድኑ የአንድነት ስሜት ጥሩ አይደለም ስለመባሉ…

” በፍፁም ! በዚህ በኩል መልካም ነገር ነው ያለው። የሚሊተሪ ክለብ ስለሆነም በየጊዜው ግምገማዎችን እናደርጋለን።እንደ ሲቪል ክለብ አይደለም ከአመራሮች ጀምሮ ሁሉም የተሰማውን መናገር ይችላል። ቡድኑን ለማቆየት የሚደረገውም ጥረት የሁሉም ተሳትፎ ያለበት ነው ፤ የቡድን መንፈሳችንም ጥሩ ነው። ”

የአሰልጣኝነት መንበሩ ጥያቄ ውስጥ ስለመግባቱ…

“ስለወንበሩ አላስብም። ቦርዱም ቢሆን እስካሁን ከጎኔ ነው ያለው። አንድ ላይ ተጋግዘን እየተነጋገርን ቡድኑን ወደ ተሻለ ቦታ ለማድረስ እየሰራን ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ባደረግነው ግምገማም ቦርዱ በርቱ ከጎናችሁ ነን የሚል ምላሽ ነው ይነበረው። ወንበሩ እንዳለ ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡