ሪፖርት | አዳማ በሜዳው በሀዋሳ ተሸንፏል

በ20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ አዳማ ከተማ  ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

ባለሜዳዎቹ በ19ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና 1-0 ከተሸነፈው ስብስብ የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ነበር ወደሜዳ የገቡት። በእንግዳዎቹ በኩል ደግሞ በሜዳቸው ባህር ዳርን አስተናግደው 1-1 ከተለያዩበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ታፈሰ ሰለሞንን እና ዳንኤል ደርቤን በማሳረፍ ብሩክ በየነ እና ምንተስኖት አበራን ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል። በጨዋታው መጀመሪያ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ኮሚሽነር መብራቱ አዲስ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ካደረጉት ሁለቱ ቡድኖች መካከል ግብ በማስቆጠር ረገድ ሀዋሳ ከተማ ነበር ቀዳሚ የሆነው። 9ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ደስታ ዮሃንስ ያሻማውን ኳስ እስራኤል እሸቱ በደረቱ ሲያወርድለት ምንተስኖት አበራ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በማስቋጠር እንግዳውን ቡድን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ አፈግፍገው መጫወትን የመረጡት ሀዋሳ ከተማዎች ከአዳማ የመሀል ክፍል ተመስርተው የሚመጡትን ኳሶች በማጨናገፍ ላይ  ትኩረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ ነበር። በሙከራ ደረጃ 34ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውስጥ ከምንተስኖት አበራ የተሰጠውን ኳስ ብሩክ በየነ ሳይጠቀምበት የቀረው የሚጠቀስ ነው። 40ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ከአዳነ ግርማ የተሻገረለትን ኳስ እስራኤል እሸቱ በቀኝ መስመር ይዞ በመግባት ወደግብ ቢያሻማውም ሮበርት ኦዶንካራ አውጥቶበታል።

ባለሜዳዎቹ በኩል ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተጭነው ቢጫወቱም አቻ መሆን አልቻሉም። 22ኛው ደቂቃ ላይ ሱለይማን መሀመድ ከአዲስ ህንፃ ሳጥን ውስጥ የተሰጠውን ኳስ ከግብ ጠባቂ  ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረ ሲሆን በድጋሜ ሱለይማን መሀመድ ከሳጥን ውጪ  ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ ግብጠባቂ ያዳነበት የቡድኑ ጥሩ የሚባል ሙከራ ነበር። የሀዋሳ ከተማዎች በጥንቃቄ የመከላከል እንቅስቃሴ እጅግ ፈታኝ የሆነባቸው አዳማዎች 32ኛዉ ላይ ከሳጥን  ውጪ በረከት ደስታ ወደ ግብ  እክርሮ የመታው እንዲሁም ብሩክ ቃልቦሬ ከርቀት በሞከሯቸው ኳሶች በመጀመሪያው አጋማሽ አቻ ለመሆን ሞክረው ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ የተመለሰውን ቡልቻ ሹራ ቀይረው በማስገባት ይበልጥ ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት አዳማዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል የተሻገረለትን ኳስ ቡልቻ በቀኝ መስመር ይዞ በመግባት ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከነበት አጋጣሚም በሁለተኛው አጋማሽ በአዳማ ከተማዎች በኩል የሚጠቀስ ነበር። ያበልጥ የመከላከል እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው የገቡት ሀዋሳዎች 68ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከተገኘ ኳስ እስራኤል እሽቱ ወደ ቀኝ መስመር ሲያሻግር ደስታ ዮሃንስ ወደ ግብ ቀይሮ የእንግዶቹን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላም አዳማዎች በፈጥሯችፕው የግብ አጋጣሚዎች ቡልቻ ሹራ ከርቀት ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂ ያዳነበት እንዲሁም ጭማሪ ደቂቃ ላይ በ92ኛው ደቂቃ በረከት ከሳጥን ጠርዝ ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂ በቀላሉ ያዳነበት የሚጠቀስ ነው። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩ ሱለይማን መሀመድ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኝውን የቅጣት ምት ቡልቻ ሹራ ወደ ግብነት ቀይሮ ልዩነቱን ማጥበብ ቢችልም የጨዋታው ቀሪ ጊዜ ተጠናቆ ሀዋሳ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ባለበት 10ኛ ደረጃ ላይ በ26 ነጥብ ሲቀመጥ ሀዋሳ በአንፃሩ በ29 ነጥቦች 8ኛ ደረጃን ይዟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡