ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር ሽረን በመርታት ወደ ድል ተመልሷል

ዛሬ ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ጅማ ላይ ስሑል ሽረን ያስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ባለሜዳዎቹ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ድሬደዋ በማቅናት በድሬዳዋ ከተማ ከተሸፈነው ስብስብ ውስጥ ዐወት ገሚካኤልን በተስፋዬ መላኩ ፣ መላኩ ወልዴን በከድር ኸይረዲን ፣ አክሊሉ ዋለልኝን በዲዲየር ለብሪ በመተካት በ4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፍ የዛሬውን ጨዋታ ሲጀምሩ ስሁል ሽረዎች በሳለፍነው ሳምንት በሜዳቸው ከቅዱስ ጊዩርጊስ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ውስጥ ግብጠባቂውን ሰንደይ ሮቲሚ በሀፍቶም ቢሰጠኝ ፣ ዲሜጥሮስ ወልደስላሴን በዮናስ ግርማይ ፣ ቢስማርክ ኦፖንግን በዐረዶም ገብረህይወት በመተካት በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጃዬ ያደረገው ታኬታ በዕለቱ ዳኞች እንዲቀየር በመታዘዙ ሌላ ቅያሪ ታኬታ እስኪመጣ ጨዋታው መጀመር ከነበረበት አስራ አምስት ደቂቃዎችን ዘግይቶ ነበር የተካሄደው፡፡ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ እና ረዳቶቻቸው በጥሩ ብቃት መርተው የጨረሱት የዛሬው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የማጥቀት ፉክክር እና የመሸናነፍ መንፈስም ነበረበት።

ባለሜዳዎቹ በዚህ የውድድር ዘመን ይጠቀሙበት ከነበረው የ4-3-3 አሰላለፍን በ4-4-2 ዳይመንድ በመቀየር ይሁን እንደሻውን ከአራቱ ተከላካዮች ፊት ለፊት መስዑድ መሀመድን ከሁለቱ አጥቂዎች ጀርባ እዲሁም አስቻለው ግርማንና ዲዲየር ሊብሬን በግራና ቀኝ መስመር የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ኦኪኪ አፎላቢ እና ማማዱ ሲዲቤን ከፊት አጥቂ በማድረግ እንደዚህ ቀደሙ ኳስን ለደቂቃዎች ከማንሸራሸር ይልቅ የሚያኙአቸውን አጋጣሚዎች በቀጥታ በመስመር አጥቂዎች በኩል በቀጥተኛ የማጥቃት እቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አንስቶ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ኦኪኪ ከሀፍቶም ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያመከነው አጋጣሚ እንዲሁም ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ምክሮ ሀፍቶም መልሶት የተተፋውን በቅርብ የነበረው አስቻለው በድጋሜ ሞክሮት አሁንም ግብ ጠባቂው ያዳነበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

የጅማዎች መሀል ክፍል ተፈጥሯዊ የተከላካይ አማካይ አለመኖሩ ሽረዎች ኳስን በሚቆጣጠሩበት ወቅት ተከላካይ ክፍሉ ቀጥታ ተጋላጭ አድርጎታል። በዚህም በአንድ ሁለት ቅብብል የጅማ ተከላካዮችን በማለፍ አረዶም ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ዳንኤል አጄዬ እንደምንም አድኖበታል። በተጨማሪም በተደጋጋሚ በቀኝ መስመር አስፍቶ ከሚጫወተው ቢስማርክ አፒያ ከሚነሱ ኳሶች ወደ ጅማ ግብ ክልል መድረስ የቻሉት ሽረዎች ይየሳሊፋ ፎፋና ተደጋጋሚ ሙከራዎች በዳንኤል አጄዬ ጥረት ውጤታማ መሆን አልቻሉም።

በ33ኛው ደቂቃ ማማዱ ሲድቤ ያሻገረውን የሽረ ተከላካዮች መዘናጋት ተከትሎ አምልጦ የገባው ኦኪኪ በሃፍቶሞ አናት ላይ ኳሳን በማሳለፍ ለራሱ የጎል አካውቱን በመክፈት ጅማን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጠረ፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላም በዕለቱ ጥሩ ይቀሳቀስ የነበረው አስቻለው ግርማ እና ማማዱ ሲድቤ ተደጋጋሚ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ቢያደርጉም ምንም እንኳን በተከላካዮች መዘናጋት ግብ ቢያስተናግድም የሀፍቶም ቢሰጠኝ የዕለቱ ድንቅ አቋም ስሑል ሽረዎች በርከት ያሉ ግቦች እንዳያስተናግዱ ረድቷቸዋል።

 

ከእረፍት መልስ እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በፈጣን እንቅስቃሴ እና በግብ ሙከራዎች የታጀበው ጨዋታው እስከ 60ኛው ደቂቃ ድረስ ሽረዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ሲሆን ከቅጣት ምቶች እንዲሁም ከመዕዘን ምት ከሚሻገሩ ተኳሶች በተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ዳንኤል አጄዬን አልፎ ግብ ማስቆጠር አልቻሉም፡፡ በሽረዎች ኳስ ቁጥጥር ምክንያት ወደ ኃላ ለማፈግፈግ የተገደዱት ጅማዎች መልሶ ማጥቃትን እንደ አማራጭ በመውሰድ ዕድሎችን በመፍጠር ወደ ግብ በመድረስ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ነበር። ይህም ሙከራቸው ፍሬ በማፍራት በ59ኛው ደቂቃ ነቅለው በአባ ጅፋር ግብ ክልል የነበሩት የሽረ ተጫዋቾች ኳስ በመነጠቃቸው በመልሶ ማጥቃት ማማዱ ሲዲቤ ለአስቻለው ያሻገረለትን አስቻለው መሬት ለመሬት በመምታት የጅማዎችን መሪነት ወደ 2-0 ከፍ ያደረገች ግብ አስቆጠሯል። ሁለተኛዋ ግብ በጊዜ እንደመቆጠሯ እና የጨዋታው ፍጥነት ከግቧ በኃላ አለመቀዝቀዙ ተጨማሪ ግቦች እንደሚቆጠሩ ቢገመትም የሁለቱ ግብ ጠባቂዎች ጥረት ተጨማሪ ግቦች ሳያስተናግድ ጨዋታው በጅማ 2-0 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ምክንያት ሆኗል።

ከዛሬው ጫወታ በኃላ ጅማ አባጅፋር ነጥቡን ወደ 31 በማሳደግ ስድስተኛ ጀረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡