ባየር ሙኒክ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረመ

ባየር ሙኒክ በኢትዮጵያ በሚከፍተው የታዳጊዎች የስፖርት ማዕከል ዙርያ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የትብብር ሰነድ ሲፈራረም በዕለቱ በታዳጊዎች መካከል በተደረገው ውድድር ኢትዮጵያ መድን የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።

በኢትዮጵያ የእግርኳስ አካዳሚ ለመክፈት ቅድመ ስምምነቶችን ለመፈፀም ከእሁድ ጀምሮ አዲስ አበባ የገቡት የባየር ሙኒክ የልዑካን ቡድን ዛሬ ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የስምምነት ፊርማ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር አድርጓል። የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጂራ እና የባየር ሙኒክ ተወካዮችም በዚህ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተዋል።

ለሦስት ዓመታት በሚቆየው በዚህ ሰምምነት መሠረት የባየር ሙኒክ በኢትዮጵያ የ17 ዓመት በታች ታዳጊዎች ማሰልጠኛ አካዳሚ የሚከፍት ይሆናል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ እግርኳስን ለማሳደግ የቴክኒክ እና የአስተዳደር ሥልጠናዎችን ባለሙያዎችን በመላክ እንደሚያወናውን የተነገረ ሲሆን የተወሰኑ በሀገር ውስጥ የሚሸፈኑ ወጪዎች ካልሆነ በቀር የአካዳሚውን ሙሉ ወጪ የጀርመነ ክለብ የሚሸፍን ይሆናል። ይሁን እንጂ አካዳሚው መቼ እና የት ይከፈታል የሚለውን ከወዲሁ መግለፅ አልተቻለም።

ከስምምነቱ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከብራዚላዊው የቀድሞ የባየር ሙኒክ አጥቂ ጂኦቫኒ ኤልበር ጋር በብሔራዊ ቡድን እና ተዛማች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በተናጥል ውይይት አድርገዋል።

በታዳጊዎች በኩል ምን እየተሰራ መሆኑን ለማሳየት በማሰብ በአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር በሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ከሚካፈሉ ቡድኖች መካከል ስምንት ክለቦች በሁለት ምድብ ተከፍለው ባካሄዱት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ መድን ለፍፃሜ ዋንጫ ደርሰው ኢትዮጵያ መድን 2-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዕለቱን ዋንጫ ከጂኦቫኒ ኤልበር እጅ ተቀብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡