ስሑል ሽረ ከደቡብ ፖሊስ ጋር የተለያየውን ግብ ጠባቂ አስፈርሟል 

በቅርቡ ቀሪ የውል ወራት እየቀሩት የተለያየው ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ስሑል ሽረን ሲቀላቀል የቀድሞ የቡድኑ ተጫዋች ጌታቸው ተስፋይን በድጋሚ አስፈርሟል።

ባሳለፍነው ዓመት በጅማ አባ ጅፋር ያሳለፈው ዳዊት በመስከረም ወር ነበር አዲስ  አዳጊው ደቡብ ፖሊስን በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅሎ የነበረ ቢሆንም ከግማሽ የውድድር ዓመት ያልተሳካ ቆይታ በኋላ መለያየቱ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ወደ ስሑል ሽረ በማምራት እስከ ዓመቱ መጨረሻ ቆይታ የሚያደርግ ይሆናል።

የቀድሞው የሐረር ቢራ እና ንግድ ባንክ ግብ ጠባቂ የዝውውር ጊዜው ከመዘጋቱ በፊት የፈረመ ቢሆንም አንዳንድ ጉዳዮች ባለማለቃቸው ዝውውሩን ያጠናቀቀው በዚህ ሳምንት ነው። ክለቡ ዓርብ ከሲዳማ ቡና ጋር ሀዋሳ ላይ ለሚያደርገው ጨዋታም ከቡድኑ ጋር አብሮ ተጉዟል።

ጌታቸው ተስፋይ ቡድኑን የተቀላቀለ ሌላው ተጫዋች ነው። የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ጌታቸው ዓምና የቡድኑ አባል የነበረ ሲሆን በድጋሚ ቡድኑን ተቀላቅሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡