ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ አራት – ክፍል አምስት)

በእንግሊዛዊው የእግርኳስ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን ደራሲነት በ2008 ለንባብ የበቃው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics ን በሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብንላችሁ እንገኛለን፡፡ በዛሬው መሠናዶም የምዕራፍ አራት አራተኛ ክፍል እንዲህ ይቀርባል፡፡

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

የሩኽልበን ወህኒ ቤት እግርኳስ ማኅበር በመስከረም ወር 1915 ራሱ ብቻ የሚተዳደርበት፥ እጥር ምጥን ያሉ ደንቦችን ያካተተ አነስተኛ መጽሃፍ አወጣ፡፡ በበርሊን ከተማ “ውድ ዋጋ” ወጥቶበት ለህትመት የበቃው ይህ የመመሪያዎች መድብል አርባ ስምንት ገጾች ያሉት፣ የተጫዋቾችን የህይወት ታሪክ የሚዳስስ፣ ከየቡድን አምበሎች ጋር የተደረጉ ቃለ መጠይቆችን የያዘ እንዲሁም ጥቂት ታክቲካዊ ውይይቶችን የሚያስነብብ ነበር፡፡ እንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ባርኒይ ሮናይ እንደጻፈው ” መጽሃፉን ከይዘቱ አንጻር ስንመዝነው ከቀደሙ እግርኳሳዊ ህትመቶች በሙሉ አዲዲስ ሃሳቦችን የቃረመ ሆኖ እናገኘዋለን፤ ከዚህ አኳያ በበርካታ ጉዳዮች ላይ አጽንኦት የሰጠ የመጀመሪያው እትም ይመስለኛል፤ በተጨማሪም ለስልጠና መማሪያነት የተጠጋ እና ልዩልዩ የእግርኳስ ታክቲካዊ አማራጮችን የሚያቀርብ ሆኖ ተጽፏል፡፡ ከተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰባስበው በእስር ቤቱ ከታጎሩ አያሌ ምሁራን የሚፈልቁ ንጥር እሳቤዎች አማካኝነት የሩኽልበን እግርኳስ ማኅበር ስነ- ጽሁፋዊ አቅሙን ሊያዳብር ችሏል፡፡

” መጽሃፉ ፈጣን መሻሻል እንዲሁም ተጨባጭ እድገት በማሳየት  ላይ በሚገኘው የሩኽልበን የከፍታ ዘመን የእንግሊዝ እግርኳስ አጨዋወት ስልት ሰፊ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ ትልቅ መጻኢ ተስፋ ሊኖር ስለመቻሉ ፍንጭ ሰጪ ሃሳቦችን አቅርቧል፡፡” ይላል፡፡ ፔንትላንድ የብላክበርን ቆይታው ባሳደረበት ተጽዕኖ ሳቢያ አጫጭር ቅብብሎችን የሚተገብር የጨዋታ ስርዓት ይመርጥ ጀመር፡፡ በሮናይ ጽሁፍ ውስጥ እንደምናየው ከሆነ ግን ይህን ለማረጋገጥ የተገኘው ማስረጃ እጅግ ውስን መሆኑን ነው፡፡ እንዲያውም በሩኽልበን ካምፕ በሃሳቦች ተከራክሮ ስምምነት ላይ የመድረስ የተለመደ ባህል አበረታቶት፣ ለውጤት ብቻ ትኩረት የመስጠት ጫና ስለሌለ አልያም ቅብብሎች በረጅሙ ወደ ፊት እንዲላኩ የሚጮኹና የሚወተውቱ ደጋፊዎች ባለመኖራቸው ምናልባትም እንግሊዛዊው አሰልጣኝ እግርኳስ እንዴት መተግበር እንደሚኖርበት የወሰነው በሩኽልበን ሳይሆን አይቀርም፡፡ 

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፔንትላንድ ወደ ብሪታኒያ ተመልሶ በደቡባዊ ምዕራብ እንግሊዝ በምትገኘው ዌስት ካንትሪ ከህመሙ በማገገም ላይ ሳለ የተዋወቃትን አስታማሚ ነርስ አገባ፡፡ ሴቲቱ በጦርነቱ ወቅት የቀድሞ ባሏ ሞቶባት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ የተሰማራችና (Voluntary Aid Detachment)  ለተባለ ተቋም የምታገለግል የህክምና ባለሙያ ነበረች፡፡ ይሁን እንጂ ፔንትላንድ በሃገሩ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሌላ ሃገር አማተረ፤ ወዲያውኑም ለ1920ው ኦሊምፒክ የፈረንሳይን ቡድን ለማሰልጠን ከስምምነት ደረሰ፡፡ በውድድሩ ፈረንሳዮች ጣልያንን በሩብ ፍጻሜው ከረቱ በኋላ በግማሽ ፍጻሜው በቼኮስሎቫኪያ ተሸነፉ፤ በፍጻሜው በተፈጠረ የሜዳ ላይ ነውጥ የአሸናፊዋ ሃገር ከኦሊምፒክ ወድድሩ መታገዷ ከመሰማቱ በፊት ፈረንሳዮች ወደ ሃገራቸው አመሩ። ምናልባት ያ ባይሆን በወቅቱ ስፔን ያነሳችውን የብር ሜዳሊያ ለማግኘት የመፋለም እጣ ያገኙ ነበር፡፡ 

ፔንትላንድ የተያያዘውን አህጉራዊ ጉዞ ቀጠለና ወደ ስፔን ተመመ፡፡ እዚያ እንደሄደ በቶሎ ሬሲንግ ሳንታንዴርን ያዘ፤ ቀጠለና ደግሞ በወር አስር ሺህ ፔሴታ እንዲከፈለው ተስማምቶ አትሌቲክን ተረከበ፡፡ በባስኩ ክለብ የመጀመሪያ ልምምድ መርኃ ግብሩም ተጫዋቾች የጫማ ማሰሪያቸውን በአግባቡ እንዲያስሩ አደረገ፡፡ ” ለመሰረታዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ስጡ! ቀሪው ቀስ በቀስ ይስተካከላል፡፡” የሚል ምክርም ለገሳቸው፡፡ ከዚያም በቢልባኦ የቀድሞ የክለቡ አሰልጣኝ ባርንስ እጅጉን የሚኮራበት እና መሰረት ጥሎለት የሄደውን የረጅም-ኳስ የጨዋታ አቀራረብ አስቀረና በምትኩ የተሳኩ ቅብብሎች ላይ የሚመረኮዘውን ስልት እንዲለመድ ተጋ፡፡ በእርግጥ የላ-ፉሪያ መሰረታዊ መስፈርቶች የሆኑት አካላዊ ጥንካሬና ቁርጠኝነት በፔንትላንድ አዲሱ አጨዋወት ውስጥ ቦታ ቢኖራቸውም ዋነኛ ግቡ ግን እርጋታና በጥልቅ ሃሳብ የሚራመድ እግርኳሳዊ ስርዓትን ማስፈን ሆነ፡፡ አሰልጣኙ ልምምድ ሲያሰራ ሲጋራ የማጨስ ሱስ ተጸናውቶት ነበር፡፡ የእርሱ ምርጫ ሁሌም ቢሆን ስርዓቱን የጠበቀ ስለመሆኑ አብዝቶ ስለሚሞግት እንደ አየር ሁኔታው ተለዋዋጭነት አለባበሱን እንዲያስተካክል እና ሱሱን እንዲያቆም ሲመከርም “እምቢኝ!”ይል አበዛ፡፡ በ1928 በወጣ የ<ኤል ኖርቴ ዲፖርቲቮ> ጋዜጣ ላይ በሚታየው ምስሉ ፔንትላንድ ወፈር ባለ ሙሉ ልብሱና ዥንጉርጉር ክራባቱ እንዲሁም በኮቱ ኪስ ውስጥ በሸጎጠው በወጉ የታጠፈ መሃረብ አማካኝነት የዘወትር <ፕሮቶኮሉ>ን እንደጠበቀ ያስታውቃል፡፡ በዚያ ላይ ያለመበገር ስሜት የሚስተዋልበት ፊቱ ኮስታራ ገጽታውን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ በፎቶው ላይ ከአፍንጫው ስር እጅብ ብሎ ከተንዠረገገው ጺሙ በታች ያለው ፈገግታም ምፀታዊ መሆኑ ግልጽ ይመስላል፡፡ ፔንትላንድ አዘወትሮ ከአናቱ ላይ ጣል የሚያደርጋት ክብ ጠፍጣፋ ባርኔጣ አለችው፤ የክት መለያውም ሆናለታለች፤ <ኤል ቦምቢን> የተሰኘ ቅጽል ስም ያገኘውም በዚህችው ኮፍያ አማካኝነት ነው፡፡ ፔንትላንድ በባህሪው በዙሪያው የሚገኙ ሰዎች በሙሉ ጠንክረው እንዲሰሩ የሚያደርግ ፣ እጅግ ስኬታማና የተለየ ሰው ነበር፡፡ 

በመጠኑ ወደኋላ አፈግፍገው የሚጫወቱ የመስመር አጥቂዎች (Inside-Forwards) የያዘው አትሌቲክ በፔንትላንድ አመራር ስር ሁለት ተከታታይ የ<ቢስካይ ውድድር ዋንጫ> እንዲሁም የ1923 <የንጉስ ዋንጫ> ድሎች ተቀዳጀ፡፡ የቢልባኦ ተጫዋቾችም የፔንትላንድን ኮፍያ ከጭንቅላቱ ላይ በመውሰድ የቆቧ አመድ ቡን እስኪሚል ድረስ እየዘለሉ ደስታቸውን የመግለጽ ባህል አመጡ፡፡ እንዲያውም በኮፓ ዴል ሬይ ፍጻሜ መጠናቂያ ገደማ ” ዝርጉ ባርኔጣ ሆይ ሶስት ደቂቃዎች ብቻ ቀሩህ!” ብለው እስከ መጮህም ደረሱ፡፡ 

በ1925 ፔንትላንድ ወደ አትሌቲክ ማድሪድ ተዘዋወረ፡፡ (ለክለቡ “አትሌቲኮ” የሚለው ስያሜ የተሰጠው በ1941 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡) ክለቡን  በተቀላቀለ በዓመቱ ቡድኑን ለንጉስ ዋንጫ ፍጻሜ አደረሰ፡፡ ቀጠለና ወደ ሪያል ኦቪዬዶ ተጉዞ የአንድ ዓመት ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ አትሌቲክ ማድሪድ ተመልሶ በ1927 <ኤል ካምፒዮናቶ ዴል ሴንትሮ> የተባለውን ዋንጫ አሸነፈ፡፡ በ1929 ማድሪድ ውስጥ በሚገኘው ኢስታዲዮ ሜትሮፖሊታኖ እንግሊዝ ስፔንን ገጥማ በባለሜዳዋ ሃገር አስገራሚ ብልጫ ተወስዶባት 4-3 በተረታችበት ጨዋታ የስፔን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆዜ ማሪያ ማቴዎስ አማካሪ ሆኖ ሰራ፡፡ በዚህም እግርኳስ ፈጣሪዋ ሃገር ከአህጉሪቱ ቡድኖች ጋር ስትጫወት ገጥሟት የማያውቀውን ሽንፈት ለመጀመሪያ ጊዜ ተከናነበች፡፡ በዚያው ዓመት መጨረሻ ፔንትላንድ ማድሪድን ለቆ ወደ ቢልባኦ አመራ፡፡ ከአራት የውድድር ዘመናት በኋላ በ1933 ወደ ማድሪድ በድጋሚ ሲመለስ አራት የላሊጋ ድሎች፣ አራት የንጉስ ዋንጫዎች እና ሶስት የቢስካይ ውድድር የአሸናፊነት ክብሮችን ሰብስቦ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እስካሁን ድረስ በባርሴሎና ክለብ እግርኳስ ታሪክ መራር ሽንፈት ሆኖ የተመዘገበውን የ1-12 የቢልባኦ ድልንም አስመዘገበ፡፡

ነገርግን በስፔን እየተስፋፋ የነበረው የእርስበርስ ጦርነት እየተፋፋመ ሲሄድ በ1936 ፔንትላንድ ሃገሪቱን ለቀቀ፡፡ ከዚያም ወደ ትውልድ ሃገሩ እንግሊዝ ተመልሶ ለአጭር ጊዜያት የብሬንትፎርድ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ ከዚያም በብሪታኒያ በዋና አሰልጣኝነት የሰራበትን ብቸኛ ክለብ ባሮው ተረከበ፡፡ ያለመታደል አልያም እርግማን መሰል ልማድ ሆኖ እንደ ብዙዎቹ ቀደምት አሰልጣኞች በተለይም ደግሞ ጂሚ ሆጋንን የመሳሰሉ ታላላቅ ሃሳባውያን የብሪታኒያ ምርጥ የእግርኳስ ባለሟሎች ሁሉ ፔንትላንድም በሃገሩ ተገቢው ክብር ተነፍጎት ባይተዋር ሆነ፡፡ አሰልጣኙ ትውልድ ሃገሩ ይልቅ በስፔኗ ቢልባኦ የከተማዋን ታላቅ ክለብ የገነባ ያህል የገዘፈ አድናቆት ይቸረዋል፡፡ እንዲያውም በ1959 ክለቡ ከቼልሲ ጋር ለሚያደርገው የመታሰቢያ ጨዋታ ተጋብዞ ወደ ቢልባኦ ሲመጣ የአትሌቲክ ልዩ የክብር አባልነት መዳሊያ ተሰጥቶታል፡፡ ከሶስት ዓመት በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይም ክለቡ በሳን ማሜስ የእርሱን መታሰቢያ ምስል አቁሞ የሽኝት ክብር አዘጋጅቶለት ነበር፡፡ 

ከፔንትላንድ በኋላ በጣልያን ከጄኔዋ እና ናፖሊ ክለቦች ጋር በአሰልጣኝነት አመርቂ ስኬት የተጎናጸፈው ዊሊያም ጋርቡት አትሌቲክን ሲረከብ ስር የሰደደው የቢልባኦ-እንግሊዛውያን የቁርኝት ባህል ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ አዲሱ አሰልጣኝም በ1935/36 የውድድር ዘመን የላሊጋውን ዋንጫ አሳካ፡፡ ይሁን እንጂ ያ መከረኛ የእርስበርስ ጦርነት ሲቀሰቀስ እርሱም ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ጣልያን ተመለሰ፡፡ በጦርነቱ የጀነራል ፍራንኮ አሸናፊ ሆኖ መውጣት በአትሌቲክ ትልልቅ አብዮቶችን አስከተለ፡፡ በመጀመሪያ “አትሌቲክ” የተሰኘው የስያሜያቸው መነሻ ቃል “አትሌቲኮ” በሚል ስፓኛ ዘዬ እንዲቀየር ተገደዱ፤ በራሳቸው ግዛት የሚገኙ ባስካውያን ተጫዋቾችን ብቻ የሚመርጡበትን የአሰራር መርህ እንዲተዉም ተደረገ፡፡ በእርግጥ አምባገነኑ መሪ ጀነራል ፍራንኮ ለክለቡ ጥላቻ አልነበረውም፤ ይልቁንም በ1950ዎቹ መባቻ ሪያል ማድሪድ መላው አውሮፓ ላይ እግርኳሳዊ ልዕልና እስኪጎናጸፍ ድረስ ከልቡ የሚደግፈው እና የእርሱ ተመራጭ ቡድኑ አትሌቲኮ ቢልባኦ ሆኖ ቆየ፡፡   

ጀነራሉ ለባስካውያን ያለው አመለካከት ወሰብሰብ ያለ መልክ ነበረው፡፡ ምንም እንኳ ባስክን እንደ አንድ ነጻ ሃገር ለማሰብ ፍቃደኝነት ባያሳይም አክራሪ የካቶሊክ ሃይማኖተኛ ከመሆናቸው ፣ የግዛት ባለቤትነት እቅድ በማራመዳቸውና ከሌሎች የሃገሪቱ ነዋሪዎች አንጻር እንግዳ የሆነ ባህሪ በመላበሳቸው እርሱና ሌሎች ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች “የ<እውነተኛዋ ስፔን> ስር ከባስኮች ግዛት ይገመዳል፡፡” የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ ባስካውያን ከስፔን ዋነኛ ወራሪ-ጦረኞች መደብ መካከል ይካተታሉ፡፡ ስለ ስፔን እግርኳስና ፖለቲካ ጥሩ መጽሃፍ የጻፈው ጂሚ በርንስ ” ጀብደኝነት የሚያይልበት ድፍረታቸው፣ ራስን መስዋዕት ለማድረግ ያላቸው ተነሳሽነት፣ ለመሪዎቻቸው የሚያሳዩት ታዛዥነት እንዲሁም ለክብራቸው ለመታገል የሚያሳዩት ዝግጁነት የመሰረታዊ እሴቶቻቸው መገለጫ ናቸው፡፡” ይላል፡፡ በአስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ከባስክ ግዛት በተገኘው የ<ሎያላው> ተጽዕኖ ፈጣሪ ኢግናሲየስ አማካኝነት የተፈጠረ፣ የካቶሊክ ሐይማኖት ላይ ሊነሱ የሚችሉ ተሃድሷዊ ተልዕኮዎችን የሚቃረን እና የእምነቱን ቀኖናዊ ትውፊት የማስቀጠል አላማ ያነገበ ስርዓት (Jesuit Order) ውስጥ ከላይ የተጠቀሱት የባስካውያን ባህሪያት የተለመዱ ናቸው፡፡ ይህ ስርዓት ሰፋ ያለ ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችሉ ነጻ የትምህርት እድሎችን በመስጠት ላይ ያተኩር ነበር፡፡ ልክ እንደ እንግሊዛውያኑ ሁሉ የኢየሱሳውያኑ ትምህርት ቤቶችም ስፖርት የሰውን ልጅ ባህሪ አዎንታዊ በሆነ መልኩ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተረድተዋል፡፡ ብዙ ትልቅ ደረጃ የደረሱ ስፖርተኞችንም አፍርተዋል፤ ከእነዚህም መካከል ይበልጡን <ፒቺቺ>፣ በቅጽል ስሙ ደግሞ <ትንሹ ዳክዬ> ተብሎ የሚታወቀው ዝነኛው ራፋኤል ሞሬኖ አራንዛዲ’ም የተገኘው እና የእግርኳስ ፍቅሩን ያሳደገው ከእነዚህ ት/ቤቶች ውስጥ በአንደኛው ነበር፡፡ ቁጥርጥር ካሉ መሃረቦች በተሰራ ኳስ ሲጫወት ያደገው ይህ ተጫዋች የአትሌቲክ ክለብ ውጤታማ አጥቂ መሆን የቻለ ሲሆን በ1920ው ኦሊምፒክም የስፔን ጀግና መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ይሁን እንጂ ተጫዋቹ ከከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱ ይልቅ ከባስክ ግዛት የተገኘ ስፔናዊ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በመሆኑ ብቻ የአምባገነኑ መሪ ጀነራል ፍራንኮ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያረፈበት <ማርካ> የተሰኘው ተነባቢ ጋዜጣ በ1953 የሃገሪቱን ትልቁ ሊግ ከፍተኛ ግብ አግቢዎችን መሸለም ሲጀምር የዚህን አጥቂ ስም ለሽልማቱ መጠሪያ እንዲሆን መረጠ፡፡ ጀነራል ፍራንኮ በአንድ በኩል የባስካውያንን ብሄርተኝነት እያከሰመ በሌላው መንገድ ደግሞ ከዚሁ ክልል የሚወጡ እግርኳስ ተጫዋቾች በሃገራዊ ማንነታቸው ላይ ድርድር የማያውቁ፣ ስፔናዊነት በጥልቀት የሰረጸባቸውና ሃገር ወዳድ እንደነበሩ በተምሳሌትነት ይጠቅሳቸዋል፡፡ እንግዲህ የ<ፉሪያ ኢስፓኞላ> ትንሳዔ ተፋጥኖ እግርኳስ በአምባገነናዊ ስርዓት መንፈስ እንዲነቃቃ የተደረገውም በዚህኛው ዘመን ነው፡፡ 

የእርስበርስ ጦርነቱ ጊዜ የአየር ኃይል አባላት በነበሩ ሰዎች ከተመሰረተውና <አቪዬሲዮን ናሽናል> ከተሰኘው ቡድን ጋር በ1939 የተጣመረውን የአትሌቲኮ ማድሪድ የወቅቱ ሁኔታ ስንቃኝ ነገሩ ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል፡፡ በጦርነቱ ስምንት ተጫዋቾቹን በሞት የተነጠቀው ክለቡ በከፍተኛ እዳ ተዘፍቆ ህልውናን የማስቀጠል ትግል ላይ ይገኝ ስለነበር ውህደት የፈጠረበት ምክንያት ተቀባይነት ማግኘት ቻለ፡፡ ይሁን እንጂ አያሌ የቡድኑ ደጋፊዎች የኅብረት ውሳኔው አስደነገጣቸው፡፡ ሲጀመርም አትሌቲኮ ማድሪድ በዋና ከተማዋ ውስጥ በሚኖሩ ባስካውያን አማካኝነት የአትሌቲክ ቢልባኦ ቅርንጫፍ እንዲሆን ታስቦና ከቢልባኦ ለራቁት የክልሉ ተወላጆች ተብሎ የተመሰረተ እንጂ በክለብ ደረጃ የራሱን ማንነት ይዞ የተቋቋመ ቡድን አልነበረም፡፡ እየቆየ ሜዳ ላይ የሚታየው የክለቡ ባህል አዲሱን ወታደራዊ አገዛዝ አጉልቶ የሚያንፀባርቅ ሆነ፤ ሊጉ ተቋርጦ እንደገና ከጀመረ አንድ ዓመት በኋላ በ1939-40 የውድድር ዘመን ጀነራል ፍራንኮ የአትሌቲኮ ማድሪዱ አሰልጣኝ ሪካርዶ ዛሞራ ላይ የሰላ ትችት ሲያቀርቡ የሁኔታው ግልጽነት ወለል ብሎ ታየ፡፡ ” በዚህ ቡድን ውስጥ የጠፋው ነገር ወኔ ነው፤ ወኔ! ቡድኑ ከዚህ የበለጠ መፋለም ይጠበቅበታል፤ ተጋጣሚዎቹን በሙሉ መርታት አለበት፡፡ አሰልጣኙም ቢሆን ከፍተኛ ብርታት ሊያሳይ ይገባዋል፤ ቡድኑ ውስጥ ጥብቅ ስርዓት ማስፈንም የእርሱ ኃላፊነት ነው፤ በየጊዜው ተጫዋቾቹን በአግባቡ ይግራቸው!” አሉ፡፡ እናም ዛሞራ እንደተባለው ሒሱን ዋጥ አድርጎ ቡድኑ  አስፈላጊው የጀብደኝነት ባህሪ እንዲኖረው ማሰነ፤ አትሌቲኮ አቬሲዮን ደ-ማድሪድም የዚያን እና የቀጣዩን ዓመት ተከታታይ የሊግ ዋንጫ አሸነፈ።

በእውነቱ የላፉሪያ ስልት ላይ በመጠኑም ቢሆን አምባገነናዊ መንፈስ ታጋብቶበታል፡፡ ሙስሊሞች ከግራናዳ እንዲወጡ ለተደረገበት ቅጽበታዊ ውሳኔ እንዲሁም በአስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስፔናውያን አትላንቲክን አቋርጠው ሜክሲኮና ፔሩን ለመውረር በፈጸሙት ጀብዱ የተሞላ ተልዕኮ የጀነራል ፍራንኮ አዲሲቷ ስፔን የፕሮፖጋንዳ መሳሪያም ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በ1939 <አሪባ> የተሰኘና የጀነራል ፍራንኮ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ እንደነበረ የሚነገርለት ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ላይ የወጣ አንድ ጽሁፍ ” ከቀደመው ጊዜ ይልቅ በአሁኑ  ወቅት <ፉሪያ ኢስፓኞላ> በሁሉም ስፔናውያን ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ አግኝቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በስፖርቱ ዓለም በተለይም በእግርኳሱ ውስጥ እጅጉን ሰርጿል፡፡ ጨዋታው ደግሞ በዓለም አቀፍ መድረክ ይበልጡን ቴክኒክ ላይ አተኩረው ለታጋይነት ቦታ የማይሰጡ ተጋጣሚዎች ላይ ስፔናውያን ምሉዕ ጀግንነታቸውን በደንብ የሚገልጹበት ሆኗል፡፡” ይላል፡፡ እንግዲህ ያን ጊዜ እንደ ሞሶሎኒዋ ጣልያን ሁሉ በፍራንኮዋ ስፔንም እግርኳስ በወታደራዊ ጥብቅ ክትትል ስር የማለፍ ፈተና ተጋረጠበት፡፡ 

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

Sunderland: A Club Transformed (2007)

Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

The Anatomy of England (2010)

Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

The Anatomy of Liverpool (2013)

Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)