“ከወልዋሎ ጋር ባለኝ የእስካሁኑ ቆይታ በጣም ደስተኛ ነኝ” ደስታ ደሙ

በዘንድሮው በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከታዩት ምርጥ ወጣት ተከላካዮች አንዱ ነው። በወንጂ ተወልዶ በሙገር ሲሚንቶ ክለብ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው ደስታ ደሙ ከመሐል ተከላካይነት በተጨማሪ በመስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችል ሲሆን ለሁለት ዓመታት የተጫወተበት ደደቢትን በመልቀቅ በአሁኑ ዘንድሮ በወልዋሎ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።

በ20 እና ከ23 ዓመት በታች የዕድሜ እርከኖች የሃገሩን ማልያ ለብሶ መጫወት የቻለው ደስታ ስለ ወልዋሎ ቆይታው እና ስለ እግር ኳስ ህይወቱ ከሶከር ኢትዮጵያ አጭር ቆይታ አድርጓል።

የታዳጊ ቡድን ቆይታህ የት ነበር ?

የመጀመርያ ክለቤ ሙገር ቢ ነው። በ2006 ሁለተኛው ቡድን ገብቼ ብዙም ሳልቆይ በቀጣዩ ዓመት ወደ ዋናው ቡድን አደግኩ። በታዳጊ የነበረኝ ቆይታ በጣም ጥሩ ነበር። በሙገር በነበረኝ የሁለት ዓመት ቆይታ ብዙ ነገር ተምሬያለው። አሁን ላለሁበበት ደረጃም የሙገር አስተዋፅኦ ትልቅ ነው።

ቀጥሎ ያመራኸው ወደ ደደቢት ነበር። የሰማያዊዎቹ ቤት ቆይታህ ምን ይመስላል?

በደደቢት በሁለቱም የውድድር ዓመት የነበረኝ ቆይታ በጣም ጥሩ ነበር። እዛ በነበርኩበት ወቅት ከብዙ አንጋፋ እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በመጫወቴ በጣም ብዙ ልምድ እንድቀስም ረድቶኛል። እነ ሥዩም ተስፋየ፣ ዓይናለም ኃይሉ፣ ጌታነህ ከበደ፣ አስራት መገርሳ፣ ብርሃኑ ቦጋለ በተለይ በመጀመርያው የደደቢት ቆይታዬ በጣም ብዙ ነገር ረድተውኛል። ከሙገር ወደ ደደቢት እንድዘዋወር የመለመለኝ ፀጋዘዓብ አስገዶምም በክለቡ ይገኝ ስለነበር ብዙ ነገር አግዞኛል። በደደቢት በብዙ ልምድ ያላቸው አሰልጣኞች ስር ስለስለጠንኩ ብዙ ነገር ተምሬያለው። በዚ አጋጣሚ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ እና (ነብሱን ይማረው) ንጉሴ ደስታን ማመስገን እፈልጋለሁ።

ባለፈው ዓመት የደደቢት ውልህ ሲጠናቀቅ በርካታ ፈላጊ ክለቦች ነበሩህ። ወልዋሎን ለመቀላቀል የወሰንክበት ምክንያት ምንድነው?

አዎ ልክ ነህ። በዛ ሰዓት በርካታ ክለቦች ይፈልጉኝ ነበር። እኔም ለውሳኔ ሳልቸኩል ተረጋግቼ ነው ሁሉንም ነገር ያደረግኩት። ዋነኛው ወልዋሎን እንድመርጥ ያደረገኝ ግን ደጋፊው እና የቡድኑ አጨዋወት ነው።

ዘንድሮ በወልዋሎ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍክ ትገኛለህ…

ከክለቡ ጋር ያለኝ የእስካሁኑ ቆይታ በጣም ጥሩ ነው። ከዓመቱ መጀመርያ አንስቶ በቡድናችን ውስጥ ያለው ስሜት ጥሩ ነው፤ ከአሰልጣኞቸችን ጋር ያለን ግንኙነት በጣም መልካም ነው። የቡድናችን ደጋፊዎችም በጣም የተለዩ ናቸው። ከዓዲግራት ድረስ እየመጡ ነው የሚደግፉን። በእያንድንዱ ጨዋታ ረጅም ጉዞ አድርገህ ቡድንህን መደገፍ ከባድ ቢሆንም እነሱ ግን እያደረጉት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ስናሸንፍም ስንሸነፍም ለኛ ያላቸው ስሜት አንድ ዓይነት ነው።

ቡድናችሁ ወልዋሎ በሁለተኛው ዙር በጥሩ መነቃቃት ላይ ነው ያለው። የቡድናቹ ስሜት ምን ይመስላል?

የመጀመርያው ዙር ቡድናችንም ጥሩ ነበር፤ ውጤቱ ያን ያህል አስከፊ አልነበረም። በሁለተኛው ዙር ግን ከዛ የተሻለ መነቃቃት አለ፤ ብዙ ለውጦች አሉ። እስካሁን ካደረግናቸው ጨዋታዎች አብዛኞቹ ማሸነፍ ችለናል። የቡድኑ መንፈስም ጥሩ ነው። ተጫዋቾችም አሰልጣኞቻችንም በጥሩ የማሸነፍ መንፈስ ላይ ነው ያለነው።

ከዚህ በፊት በእግር ኳስ ህይወትህ ከተጫወትክባቸው ቡድኖች በተሻለ ደጋፊ ባለው ቡድን እና ስታድየም ነው እየተጫወትክ ያለኸው። በርካታ ደጋፊ ፊት መጫወት እንዴት አየኸው?

በባዶ ስታድየም መጫወት እና በበርካታ ስቴድየም ታጅቦ መጫወት ብዙ ልዩነት አለው። በደጋፊ ፊት ስትጫወት ብዙ ነገር ታገኛለህ። በጣም ትነሳሳለህ። ከዛ ባለፈ በጣም ከባድ ነገሮች ተቋቁመህ እንድትጫወት ያደርግሃል። በደጋፊ ፊት መጫወት ጥሩ ብትጫወት ያበረታታሃል መጥፎ ብትጫውትም ያርምሃል እና በደጋፊ ፊት መጫወት ልዩ ስሜት አለው።

የኢትዮጵያን ማልያ ለብሰህ መጫወት ጀምረሃል፤ ግብም አስቆጥረሃል። ስሜቱ እንዴት ነበር?

ስሜቱን በቃላት መግለፅ በጣም ከባድ ነው።
የአንድ እግርኳስ ተጫዋች የመጨረሻ ስኬቱ ብሄራዊ ቡድን መጫወት ነው። የሃገርህ ማልያ ለብሰህ ስትጫወት ልዩ ስሜት ነው ያለው። ከማሊ ጋር ስንጫወት ካስቆጠርኳት ግብ በኃላ በጣም ልዩ ስሜት ነው የፈጠረብኝ። በአጠቃላይ የብሄራዊ ቡድን ቆይታዩ አሪፍ እና ብዙ ነገር የተማርኩበት ነው።

በርካታ ቦታዎች ላይ መጫወት ትችላለህ። ይሄን እንዴት አዳበርከው?

ልምዴ የጀመረው ከሙገር ታዳጊ ቡድን ነው።
በሙገር ቆይታዬ ፋሲል ጉታ እና ኤልያስ የሚባሉ አሰልጣኞች በርካታ ቦታዎች ላይ ያሰልፉኝ ነበር። መሐል ተከላካይ፣ መስመር ተከላካይ እና የመስመር ተጫዋች ሆኜ መጫወት የጀመርኩት ከታዳጊ ጀምሮ ነው። ከዛ በኋላ ደግሞ ወደ ሙገር ዋና ቡድን ሳድግ ዋና አሰልጣኝ ግርማ ሐብተዮሐንስም በተመሳሳይ በርካታ ቦታዎች ላይ ያጫውቱኝ ነበር።

እስካሁን ድረስ ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር ተጣምረሃል። ካንተ ጋር ሲጣመር ምቾት የሚሰማህ ማን ነው?

በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። ምክንያቱም ከበርካታ ትላልቅ ተከላካዮች ጋር ተጣምሬ ተጫውቻለው። ግን አንድ ምረጥ ካልከኝ ከዓይናለም ኃይለ ጋር ስጣመር ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ከሱ ጋር በተጫወትኩበት አጭር ጊዜ ብዙ ነገር አስተምሮኛል። በዛ ላይ ጥሩ መሪ እና ታጋይ ተጫዋች ነው።

የወልዋሎ ውልህ በዚህ ዓመት ነው የሚያልቀው። የቀጣይ ዓመት እቅድህ ምንድነው? ቀጣይ ዓመት በወልዋሎ ማልያ እናይሀለን?

አሁን ባለው በብዙ ነገር ከወልዋሎ ጋር በጣም ደስተኛ ነኝ። ስለ ቀጣይ ዓመት ቆይታዬ ግን አሁን ላይ መወሰን ከባድ ነው። ውሌ ሲያልቅ የምናየው ይሆናል ።

ከሃገር ውስጥ ተጫዋቾች አርዓያህ ማን ነው?? ማንንስ ታደንቃለህ?

እግር ኳስ ስጀምር በመስመር ተከላካይነት ስለሆነ የስዩም ተስፋየ አድናቂ ነኝ። አርዓያዬ ደግሞ አስቻለው ተስፋዬ የሚባል የሰፈሬ ልጅ ነው። ታዳጊ እያለው እሱን እያየሁ ነው ያደግኩት።

በእግር ኳስ ህይወቴ ትልቅ ድርሻ አላቸው፤ ደግፈውኛል ምትላቸው ሰዎች ..

በመጀመርያ እዚ ደረጃ ላደረሰኝ እግዚአብሔር አመሰግነዋለው። በእግር ኳስ ህይወቴ ድጋፍ ያደረጉልኝ በጣም በርካታ ሰዎች አሉ። ወንደወሰን ዓለሙ፣ በሙገር ያሰለጠኑኝ ፋሲል እና ኤልያስን እንዲሁም አሰልጣኝ ግርማ ሐብተዮሐንስን ማመስገን እፈልጋለው። በዚህ አጋጣሚ የእግር ኳስ ህይወቴ ላይ እገዛ ያደረጉልኝ ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። በተጫወትኩባቸው ክለቦች ላይ ድጋፍ ያደረጉልኝ ግለሰቦች ሁሉ ማመስገን እፈልጋለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: