የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 3-3 ደቡብ ፖሊስ

የባህር ዳር ከተማ እና የደቡብ ፖሊስ ጨዋታ 3-3 ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ይህን ብለዋል
“የሰራናቸው ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ ብዙ ማለት አልፈልግም። ነገር ግን ኳስን በመቆጣጠር የተሻልን ነበርን። በስተመጨረሻ የሰራናቸው ስህተቶች ደግሞ ዋጋ አስከፍለውን አቻ ወተናል። ቡድኔ ከመሸነፍ ስለመጣ ጥሩ ሙድ ላይ አልነበረም። ይህንን ነገር ደግሞ ለመቅረፍ እና ቶሎ ወደ አሸናፊነት ስሜት ለመመለስ የበዛ ፍላጎት ነበረን። ይህ ጉጉት ደግሞ ስህተቶችን እንድንሰራ አድርጎናል።”

ስለ ተፈጠሩት ስህተቶች

“እንደተመለከታችሁት የተፈጠሩት ስህተቶች የአሰልጣኝ ችግር የፈጠረው አይደለም። በተጨዋቾች የግል ስህተት የተፈጠረ እንጂ። በአጠቃላይ ግን ስህተቶች በየአጋጣሚው የሚፈጠሩ ናቸው።”

ከቡድኑ ራሳቸውን ስላነሱበት ጉዳይ

“እስካሁን ከቡድኑ ጋር ቆይታ አድርጊያለው። ነገር ግን ከአሁን በኋላ ይበቃኛል። የስራ አስፈፃሚውም ይረዳኛል ብዬ አስባለው። ስለዚህ ከዚህ ሰዓት በኋላ ከቡድኑ በራሴ ፍቃድ ለቅቄያለው። አንድ ዓመት ከስምንት ወር ከጎኔ ለነበሩ ደጋፊዎች ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው። ቡድኑ አካባቢ ያሉት ነገሮች ደስ አይሉም። የእኔ መውጣት ቡድኑን የሚጠቅመው ከሆነ ደስ ይለኛል። ነገ ለክለቡ የስራ አስፈፃሚ በራሴ ፍቃድ መልቀቄን በደብዳቤ እገልፃለው።”

ስለ ውሳኔያቸው ምንጭ

“በአጠቃላይ መናገር የምፈልገው ይህንን ብቻ ነው። ቡድኑ አካባቢ ያለው መንፈስ ጥሩ አይደለም። እኔም በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መስራት አልችልም። ይህ ጉዳይ ትልልቅ ቡድኖች ላይም የሚያጋጥም ነገር ነው። ለአሁን ግን በራሴ ሃላፊነት ከቡድኑ ተለያይቻለው። ወደ ፊት ግን ለቡድኑ ጥሩ ነገር እመኛለው።”

በመጨረሻ

” በቀጣይ ባህር ዳር ከላይ ተቀምጦ ማየት እፈልጋለው። ብዙ ደጋፊዎች መስዋዕትነት ከፍለውለታል። ከኔ በኋላም የሚመጣው አሰልጣኝ ጥሩ እድል እንዲገጥመው እመኝለታለው። ከጎኔ ለነበሩ ሁሉ ግን አሁንም ደግሜ ደጋግሜ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ።”

” በጨዋታው ሶስት ነጥብ ይገባን ነበር” ገብረክርስቶስ ቢራራ – ደቡብ ፖሊስ

ስለ ጨዋታው

“በሁለቱም ቡድኖች በኩል ነፃ ጨዋታ ነበር የታየው። ስድስት ጎል የተቆጠረውም ነፃ ጨዋታ ስለነበር ነው። እኛ የትም ሜዳ ሄደን ስንጫወት ለመከላከል ቅድሚያ አንሰጥም፤ አጥቅተን ነው የምንጫወተው። ምክንያቱም በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ አካባቢ ስላለን ማሸነፍ አለብን። በአጠቃላይ ጥሩ ጨዋታ ነበር።”

ስለተቆጠረባቸው ግቦች

” እግር ኳስ ሁል ጊዜ ተለዋዋጭ ነው። ዛሬ የተቆጠሩብን ጎሎች አብዛኛው መነሻቸው ከቆመ ኳስ ነው። ዛሬም ይዤ የመጣሁት ስብስብ የተሟላ አልነበረም። ምክንያቱም ሶስት ተጨዋቾችን በጉዳት አሳርፈን ነበረ። ይህ ይህ ተደማምሮ ግቦች በአየር ላይ እንድናስተናግድ አድርጎናል።”

ስለ ውጤቱ

” ዛሬ ሶስት ነጥብ አጥተናል ብለን ነው የምናስበው። ምክንያቱም 3-2 መርተን ነበር። ከኋላ ተነስተን እንደመምራታችን ሶስት ነጥብ ይገባን ነበር። በተለይ ግን ሶስተኛው ጎል የተቆጠረብን መንገድ አላስደሰተኝም። የቅጣት ምቱ ሲመታ ያሳየነው የአቋቋም ስህተት ዋጋ አስከፍሎናል እንጂ ማሸነፍ ነበረብን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡