ሴቶች 1ኛ ዲቪዚዮን | አዳማ ወሳኙን ጨዋታ አሸንፎ መሪነቱን ሲቆናጠጥ መከላከያ እና ሀዋሳ በጎል ተንበሽብሸዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀምር የአዳማ ከተማ እና ንግድ ባንክ የዓመቱ እጅግ ወሳኝ ጨዋታ በአዳማ አሸናፊነት ተጠናቋል። ሀዋሳ እና መከላከያ ደግሞ ተጋጣሚዎቻቸውን በሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፈዋል።

ሀዋሳ ከተማ 7-1 አርባምንጭ ከተማ

(በቴዎድሮስ ታከለ)

ረፋድ 4:00 ላይ ሀዋሳ ከተማ አርባምንጭ ከተማን ጋብዞ 7-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ አጀማመራቸው መልካም ይመስል የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች በተለይ በቀኝ በኩል በተሰለፈችው ፀጋነሽ ወራና አማካኝነት ተደጋጋሚ እድሎችን ቢያገኙም የአጥቂዎቻቸው ድክመት ግብ ማስቆጠር እንዳይችሉ ዳርጓቸዋል፡፡ በሂደት በቀኝ በኩል ከተከላካይ ቦታ በመነሳት በካሰች ፍሰሀ እንደሰሞነኛ አጨዋወታቸው ለማጥቃት የሞከሩት ሀዋሳዎች በአጥቂዋ ምርቃት ፈለቀ አማካኝነት የግብ አጋጣሚን አግኝተው መጠቀም አልቻሉም። መሠረት ማቲዮስ 17ኛው ደቂቃ ላይ በአርባምንጭ በኩል መልካም አጋጣሚን አግኝታ መጠቀም ሳትችል ቀርታለች 20ኛው ደቂቃ ላይ ለአርባምንጭ የተከላካይ ክፍል ፈተና የነበረችሁ አጥቂዋ መሳይ ተመስገን 20ኛ ደቂቃ ላይ ከአርባምንጯ ተከላካይ ዝናቧ ሽፈራው ጋር መሀል ሜዳው ላይ ተጋጭተው የወደቁ ሲሆን በህክምና ባለሙያዎች ህክምና ተደርጎላቸው በድጋሚ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ 

26ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ በግራ በኩል ያሳለፈችላትን ኳስ ካሰች ፍሰሀ ወደ ግብነት ለውጣ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጋለች። 33ኛው ደቂቃም ላይ በድጋሚ ምርቃት ተመሳሳይ አይነት ኳስ ለመሳይ አቀብላት መሳይ ፍጥነቷን ተጠቅማ ግብ አስቆጥራ መሪነቱን ወደ 2-0 አሳድጋዋለች፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ልዩነት ስትፈጥር የነበረችው መሳይ ተመስገን በድጋሚ ግብ አስቆጥራለች። 37ኛው ደቂቃ ላይ ቱሪስት ለማ አርባምንጮች ለእረፍት በባዶ ግብ እንዳይወጡ ያደረገች ጎል አስቆጥራ በ3-1 ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ ሀዋሳዎች ብልጫን በወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ ምርቃት ፈለቀ በርካታ የግብ ዕድሎችን አግኝታ ከፊሉን በቀላሉ ስታመክን በሌላ አጋጣሚ ደግሞ በግብ ጠባቂዋ ተስፋነሽ ተገኔ ጥረት ከሽፈውባታል፡፡ 53ኛው ደቂቃ መሳይ ተመስገን ያቀበለችውን ኳስ ምርቃት ፈለቀ አግብታ የሁለተኛውን አጋማሽ የጎል አካውንት መክፈት ችላለች። አንድም ሙከራን አርባምንጮች ማድረግ ባልቻሉበት በዚህ አጋማሽ ሀዋሳዎች 79ኛው ደቂቃ ከግራ በኩል ከቅጣት ምት በረጅሙ የተሻገረን ኳስ ምርቃት አስቆጥራ ወደ 5-1 ከፍ ስታደርግ 87ኛው ደቂቃ በሳራ ኬዲ 90ኛው ደቂቃ በነፃነት መና ተጨማሪ ግቦችን አክለው ሀዋሳ ከተማ 7-1 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

አዳማ ከተማ 2-1 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

(በዳንኤል መስፍን)

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የተካሄደው ተጠባቂው የአዳማ ከተማ እና የንግድ ባንክ ጨዋታ በአዳማ ከነማዎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው ጅማሬ አንስቶ ባለሜዳዎቹ አዳማዎች በፈጣን እንቅስቃሴ እና ኳሱን ተቆጣጥረው በግሩም የጨዋታ ፍሰት በተደጋጋሚ የንግድ ባንክን በር ሲፈትሹ ቢቆዩም የጎል እድል በመፍጠር ግን አልቻሉም ነበር። ይልቁንም ብልጫ የተወሰደባቸው ንግድ ባንኮች በአንድ አጋጣሚ ሽታዬ ሲሳይ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ጥሩ የግብ እድል አግኝታ የነበረ ቢሆንም ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ጨዋታው እጅግ ተጠባቂ እንደመሆኑ መጠን ጥንቃቄ የበዛበት አጨዋወት መከተልን ሁለቱም ቡድኖች ምርጫቸው ያደረጉ ሲሆን በዚህም በሁለቱም በኩል ጠንካራ የሆኑ የጎል ሙከራዎችን ሳንመለከት የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሊሄድ ችሏል።

32ኛው ደቂቃ የጨዋታውን መንፈስ የቀየረ ጎል አዳማ ከነማዎች አስቆጥረዋል። ከመሐል ሜዳ አንስቶ የተመሰረተው ኳስ ከንክኪዎች በኋላ በቀኝ መስመር የነበረችው ሴናፍ ዋቁማ ጋር ደርሶ ነፃ አቋቋም ላይ ለምትገኘው ሰናይት ቦጋለ ያቀበለቻትን ሰናይት በግራ እግሯ ደግፍ አድርጋ የአዳማን ቀዳሚ ጎል ማስቆጠር ችላለች። ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተነቃቁት ንግድ ባንኮች ብዙም ሳይቆይ ከቅጣት ምት ሽታዬ ሲሳይ የግብ አጋጣሚ ብትፈጥርም ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ሊወጣባት ችሏል። ብዙ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት እና ጨዋታውን የሚገልፁ ነገሮችን መመልከት ሳንችል ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ንግድ ባንኮች ረጃጅም ኳስ መጠቀማቸው በመጀመርያው አጋማሽ የብርትካንን እንቅስቃሴ ከማጥፋቱም ባሻገር የሚነጥቁትን ኳሶች አደራጅተው ለመሄድ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የሚሰሩት ስህተት ኳሱን እየተነጠቁ በመልሶ ማጥቃት ጫና እንዲፈጠርባቸው አድርጓል። በፍጥነት ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ የሚገቡት አዳማዎች የግብ ዕድል አይፍጠሩ እንጂ የንግድ ባንክን ተከላካይ ይረብሹ እንደነበረ ማስተዋል ተችሏል። በዚህ ሂደት ውስጥ ነበር 62ኛው ደቂቃ ላይ ሽታዬ ሲሳይ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን በአዳማ ተከላካይ እና ግብጠባቂዎ እምወድሽ መካከል በተፈጠረ አለመናበብ ክፍተቱን ተጠቅማ ረሂማ ዘርጋው ንግድ ባንኮችን አቻ ማድረግ ችላለች። ብዙም ሳይቆይ ሽታዬ ሲሳይ የግብ ዕድል አግኝታ የነበረ ቢሆንም ግብጠባቂዋ እምወድሽ አድናበታለች።

ጨዋታው በተመጣጣኝ ፉክክር ቀጥሎ 72ኛው ደቂቃ አዳማዎች ከርቀት ያገኙትን ቅጣት ምት ሎዛ አበራ ወደ ጎል ስትመታው የግቡ አግዳሚ የመለሰውን በኳሱ ቅርብ ርቀት የነበረችው ሴናፍ ዋቁማ አግኝታ በግንባሯ በመግጨት ጣፋጭ የሆነ ሁለተኛ ጎል ለአዳማ ከነማ አስቆጥራለች። በቀሩት ደቂቃዎች ፌደራል ዳኛ ቢንያም ባህሩ ጨዋታውን የመራበትን ብቃት ከማድነቅ ውጪ የረባ ነገር ሳንመለከት ተጠባቂው ጨዋታ በአዳማ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

መከላከያ 6-2 ቅዱስ ጊዮርጊስ

(በአምሀ ተስፋዬ)

8:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመው መከላከያ 6-2 አሸንፏል። የህሊና ፀሎት በማድረግ በተጀመረው ጨዋታ ገና ከጅምሩ የማጥቃት ጫና መፍጠር የቻሉት መከላከያዎች ጎል ማግኘት የቻሉትም በቶሎ ነበር። በ4ኛው ደቂቃ መዲና ዐወል ከግብ ክልሉ ኳስን ለማዳን የወጣችው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂን በማለፍ ያመቻቸችላትን ኳስ የምስራች ላቀው አክርራ ስትመታ ግብ ጠባቂዋ ብታድነውም ከመስመር አልፏል በማለት የእለቱ ዳኛ በማፅደቅ ነበር የመጀመርያ ጎላቸውን ያገኙት። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶችም በተመሳሳይ ሒደት አቻ ሆነዋል። ያገኙትን ቅጣት ምት ሶፋኒት ተፈራ መትታ የግቡን የላይኛውን አግዳሚ ገጭቶ መሬት ነጥሮ የወጣውን ኳስ የእለቱ ዳኛ ከመስመር አልፏል በማለት ፀድቋል።

ከጎሎቹ በኋላ መከላከያዎች በተደጋጋሚ ወደ ጎል መድረሳቸውን በመቀጠል በ16ኛው ደቂቃ ላይ ከመዓዘን የተሻገረውን ኳስ መዲና ዐወል በግንባሯ ገጭታ ጦሩን ወደ መሪነት መልሳለች። መዲና በድጋሚ በ23ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ18 ሜትር ርቀት አክርራ በመምታት የመከላከያን ልዩነት ስታሰፋ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በረጅሙ የተለየየጋውን ኳስ የምስራች ላቀው ከግብ ጠባቂዋ ቀደማ በመድረስ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረችው አረጋሽ አሻግራት በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው አረጋሽ ወደ ጎልነት ቀይራዋለች። የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቂያ ላይ ደግሞ ሔለን ሰይፉ የመከላካያን ግብ ወደ አምስት ከፍ ማድረግ ችላለች።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በእንቅስቃሴ ተሽለው የቀረቡት ጊዮጊሶች ልዩነቱ ለማጥበብ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። በተለይም በ51ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያ ተጫዋች ሄለን ሰይፉ የቀይ ካርድ ሰለባ መሆኗን ተከትሎ ለቅዱስ ጊዮርጊሶች ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር። በ72 ኛው ደቂቃ ላይም ብርሃን ኃይለሥላሴ ከርቀት አስቆጥራ ልዩነቱን አጥባለች። ሆኖም ወደ ፊት ተስበው ሲጫወቱ የነበሩት ጊዮርጊሶች በ82ኛው ደቂቃ ከጨዋታ ውጭ ነው በሚል ተዘናግተው ሲቆሙ መዲና ዐወል ከማሐል አፈትልካ በመውጣት በግብ ጠባቂዋ አናት ላይ ኳሱን በመስደድ ለራሱ ሶስተኛ ለቡድኑ ስድስተኛውን ጎል አስቆጥራ ጨዋታውም በመከላካያ 6-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: