ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ወልቂጤ መሪነቱን ከመድን ተረክቧል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ቅዳሜ ፣ እሁድ እና ዛሬ ሲከናወን መድን እና ኢኮስኮ ሽንፈትን አስተናግደዋል ፤ ወልቂጤ ደግሞ ድል አስመዝግቦ መሪነቱን መልሶ ተቆናጧል።

ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ረፋድ 4:00 ላይ በዕኩል 32 ነጥቦች ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ኢኮስኮ እና ወልቂጤ ከተማ የተገናኙበትን ጨዋታ ወልቂጤዎች በአቡዱልከሪም ወርቁ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል በማሸነፍ ወደ ምድቡ መሪነት ከፍ ያሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ6ኛው ደቂቃ የኢኮስኮ ተጫዋች ኳስ በራሱ የግብ ክልል ውስጥ በእጁ በመንካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት አብዱልከሪም ወርቁ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ በተሰጠባቸው ፍፁም ቅጣት ምት ደስተኛ ያልነበሩት ኢኮስኮዎች በጉዳዩ ዙርያ ክስ ካስያዙ በኋላ ነበር ጨዋታው የቀጠለው፡፡

በግቧ መቆጠጠር የተነቃቁ የሚመስሉት ወልቂጤዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን መድረስ ችለዋል ፤ በተለይም አብዱልከሪም በ10ኛው እንዲሁም በ26ኛው ደቂቃ ያደረጋቸው አስደንጋጭ ሙከራዎች በኢኮስኮ ተጫዋቾች እንዲሁም በግብ ጠባቂው ጥረት ግብ ከመሆን ዳኑ እንጂ መሪነታቸውን ከፍ ሊያደርጉበት የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

በተመሳሳይ በ27ኛው ደቂቃ ወልቂጤዎች ከማዕዘን ያሻሙትን የግራ መስመር ተከላካያቸው በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ ሲልካት የግቡን ቋሚ የለተመችበት ኳስ ሌላዋ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች፡፡ ሳይጠበቅ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ በተቆጠረባቸው ግብ የተረበሹ የሚመስሉት ኢኮስኮዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ፤ በ30ኛው ደቂቃ ያገኙትን ቅጣት ምት ተጠቅመው የወልቂጤ ተጫዋቾች በተዘናጉበት ቅፅበት በፍጥነት በመጀመር አባይነህ ፊኖ ወደ ግብ ሊሞክር በተዘጋጀበት ቅፅበት ኤሚክሬል ቢሌንጌ የግብ ክልሉን በፍጥነት ለቆ በመውጣት ሊያድንበት ችሏል፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎች 45 የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች የተሻሉ የነበሩት ኢኮስኮዎች በ38ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ያሻሙት ኳስ በወልቂጤ ተከላካዮች ተገጭቶ ሲመለስ ከሳጥን ውጪ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሄኖክ አወቀ በቀጥታ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ቤሊንጌ በተመሳሳይ በግሩም ሁኔታ ሊያድንበት ችሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በአንድ ግብ ልዩነት እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት ኢኮስኮዎች በሁለተኛው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ላይ ፍፁም የበላይነት ወስደው መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በዚሁ አጋማሽ በወልቂጤዎች በኩል ደምቆ የዋለው ግብ ጠባቂው ቤሊንጌ ግን የሚቀመስ አልሆነም። በዚሁ አጋማሽ ግብ ጠባቂው በርካታ የግብ ሙከራዎችን በግል ጥረቱ ሊያመክን ችሏል። በተለይም በ54ኛው አባይነህ ፊኖ በግንባር ገጭቶ የሞከረው እንዲሁም በ84ኛው እና በ85ኛው ደቂቃ ላይ ዓዲስአለም ደሳለኝ እና አባይነህ ፊኖ አከታትለው ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸውን ሙከራዎች በግሩም ሁኔታ ማምከን ችሏል፡፡

በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ወልቂጤዎች ያገኟቸውን አጋጣሚዎች አህመድ ሁሴን በሁለት አጋጣሚዎች እንዲሁም አብዱልከሪም ወርቁ በአንድ አጋጣሚ በሚያስገርረም ሁኔታ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡ ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ወልቂጤዎች በዚህ ሳምንት የምድቡ መሪ ኢትዮጵያ መድን ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 35 ከፍ በማድረግ ምድቡን መምራት ጀምረዋል፡፡

የጨዋታውን ዋና ዋና ሁነቶች በዩቲዩብ ቻነላችን ይመልከቱ | You Tube

ቅዳሜ ሶዶ ላይ ወላይታ ሶዶ ከኢትዮጵያ መድን ጋር የተገናኙበት ሌላው የምድቡ ተጠባቂ ጨዋታ ነበር። የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ የመድን ግብ ጠባቂ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠሩ በሶዶ መሪነት ተጠናቋል። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ብሩክ አማኑኤል በ58ኛው ደቂቃ ላይ የሶዶን ሁለተኛ ግብ ከመረብ ማዋሀድ ችሏል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የመድን ግብ ጠባቂ የሆነው ተስፋ ሚካኤል በሰራው ስህተት ከሜዳ በቀይ ካርድ ወጥቷል። መድን መሸነፉን ተከትሎ መሪነቱን ለወልቂጤ አስረክቧል።

አዲስ አበባ ኦሜድላ ሜዳ ላይ የተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ እና የካ ክፍለ ከተማ ጨዋታ በየካ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ብቸኛውን የማሸነፊያውን ጎል ዳኛቸው አስቆጥሯል። በሁለተኛው የውድድር አጋማሽ መሻሻል ያሳየው የካ ክፍለ ከተማ 12 ነጥቦችንም መሰብሰብ ችሏል።

ዱራሜ ላይ ሀምበሪቾን ከዲላ ያገናኘው ጨዋታ ደግሞ 65ኛው ደቂቃ ላይ ዘካርያስ ፍቅሬ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ በአምበሪቾ አሸናፊነት ተደምድሟል። በጨዋታው የዲላ ተጫዋች በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ይህን ተከትሎ የዲላ እና የአምበሪቾ አመራሮች ለሶከር ኢትዮጽያ እንደገለፁት አወዳዳሪው አካል ለውድድሩ ትኩረት በመስጠት የሚመድባቸውን ዳኞች እንዲገመግም በማሳሰብ በዕለቱ ዳኝነት ደስተኛ እንዳልነበሩ ገልፀዋል።

ሀላባ ላይ ሀላባ ከተማ ከነገሌ አርሲ ባደረጉት ጨዋታ ሀላባ 1-0 ማሸነፍ ችሏል። በዘንድሮ ውድድር ዓመት መቀዛቀዝ የታየበት ኤፍሬም ቶማስ በ52ኛው ደቂቃ ላይ ባገባው ብቸኛ ግብ ነበር ጨዋታውን በድል የተወጡት።

ድሬዳዋ ላይ ናሽናል ሲሚንት ከድሬዳዋ ፖሊስ ባደረጉት ጨዋታ ድሬዳዎ ፖሊስ 2-0 አሸንፏል። ፈርዓን ሰይድ በ45ኛው እና ዘርዓይ በ87ኛው ደቂቃ ግቦቹን ለድሬዳዋ ፖሊስ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: Content is protected !!