ሪፖርት | ባህር ዳር እና ወልዋሎ ነጥብ ተጋርተዋል

በ26ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባህር ዳር ላይ የተገናኙት ባህር ዳር ከተማ እና ወልዋሎ ዓ/ዩኒቨርስቲ ጨዋታቸውን 0-0 አጠናቀዋል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች በ25ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ወደ መቐሌ አምርተው በደደቢት 5-2 ከተሸነፉበት ጨዋታ ሰባት ተጨዋቾችን በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ሃሪስተን ሄሱ፣ አሌክስ አሙዙ፣ሄኖክ አቻምየለህ፣ ሚካኤል ዳኛቸው፣ ዜናው ፈረደ፣ ጃኮ አራፋት እና ወሰኑ ዓሊን በምንተስኖት አሎ፣ ወንድሜነህ ደረጄ፣ አቤል ውዱ፣ ዳንኤል ኃይሉ፣ ፍቃዱ ወርቁ፣ እንዳለ ደባልቄ እና ልደቱ ለማ ተክተው ገብተዋል። ተጋባዦቹ ወልዋሎዎች ደግሞ ከወላይታ ዲቻ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት የባለፈው ሳምንት ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ዳንኤል አድሀኖምን እና ብርሃኑ አሻሞን በእንየው ካሳሁን እና አ/ራህማንፉሴይኒ ተክተው ገብተዋል።

ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር በተስተዋለበት የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጋባዦቹ ወልዋሎዎቸ ተሽለው ሲንቀሳቀሱ ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ደግሞ ተዳክመው ታይተዋል። በስምንተኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ሙከራ ያስተናገደው ጨዋታው ዳንኤል ኃይሉ ከመሃል ሜዳ ለኤልያስ አህመድ አቀብሎት ኤሊያስ በሞከረው የርቀት ኳስ ግብ ለማስተናገድ ተቃርቦ ነበረ። በደቂቃ ልዩነት ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ መስጠት የፈለጉ የሚመስሉት ወልዋሎዎቸ በአ/ራህማንፉሴይኒ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው ምንተስኖት አሎ አምክኖባቸዋል። ባህር ዳሮች እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የሜዳቸው ላይ ጨዋታዎች ኳስ መቆጣጠር ቢሳናቸውም አልፈው አልፈው በሚያደርጉት ፈጣን የመስመር ላይ ሽግግር ግብ ለማስቆጠረ ሞክረዋል። በዚህም በ13ኛው ደቂቃ አስናቀ ሞገስ በግራ መስመር በኩል ያገኘውን ኳስ ይዞ በመግባት ጥሩ ሙከራ አድርጎ ነበር።

ከዚህኛው ሙከራ በኋላ እጅጉን የተነቃቁት ቢጫ ለባሾቹ ጥቃቶችን ከየአቅጣጫው ሲሰነዝሩ ተስተውሏል። በተለይ በግራ መስመር በኩል በተሰለፈው ፉሴይኒ አማካኝነት ወደ ፊት ሲያመሩ የነበሩት ወልዋሎዎች ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በዚህም በ27ኛው ደቂቃ ፉሴይኒ ከመስመር በመነሳት እየገፋ የሄደውን ኳስ አክርሮ መቶ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ጥሯል። ባለሜዳዎቹን ኳስ ከግብ ክልላቸው መስርተው እንዳይወጡ ሲያደርጉ የነበሩት ተጋባዦቹ በ36ኛው ደቂቃ ዳግም ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል በፕሪንስ ሰቨሪንሆ አማካኝነት ደርሰው ሙከራ አድርገዋል።

ከሁለት ደቂቃ በኋላ ከጥሩ ቦታ የቅጣት ምት ያገኙት የጣናው ሞገዶች አጋጣሚውን በዳንኤል ሃይሉ አማካኝነት ወደ ግብነት ለመቀየር ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጥሩ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ፉሴይኒ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው በሞከረው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር።

በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ፍክክር ያስመለከተው የሁለተኛው አጋማሽ በጅማሮ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ከሁለቱም ቡድኖች በኩል አስተናግዷል። ገና እንደተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ በፈጣን ሽግግር ወደ ባህር ዳሮች የግብ ክልል ያመሩት ወልዋሎዎች በእንየው ካሳሁን አማካኝነት አስደንጋጭ ሙከራ ሰንዝረዋል። በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ተነቃቅተው የገቡት ባህር ዳሮች በበኩላቸው ከአራት ደቂቃ በኋላ በደረጄ መንግስቱ አማካኝነት በሞከሩት የቅጣት ምት እጅጉን ግብ ለማስቆጠረ ተቃርበው ነበረ። ከደቂቃ በኋላም ዳግም ወደ ወልዋሎዎች የግብ ክልል ያመሩት ባለሜዳዎቹ በመስመር አጥቂያቸው እንዳለ ደባልቄ አማካኝነት ሌላ ሙከራ ሰንዝረው መክኖባቸዋል።

በተቃራኒው ወደ ግብ ክልላቸው አፈግፍገው ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት የአሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ ተጨዋቾች በመልሶ ማጥቃት ብቻ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በ63ኛው ደቂቃም ፕሪንስ ከመሃል ሜዳ አክርሮ በመታው ነገር ግን የግቡን አግዳሚ ታኮ በወጣው ኳስ ሳይታሰብ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበረ። ከአምስት ደቂቃ በኋላ የቅጣት ምት ያገኙት ተጋባዦቹ አጋጣሚውን ወደ ጎልነት ለመቀየር በሪችሞንድ አዶንጎ አማካኝነት ጥረው መክኖባቸዋል።

ግብ ጠባቂን ጨምሮ አራት ተጨዋቾችን ብቻ በተጠባባቂ ወንበር ያስቀመጡት ባህር ዳሮች ባላቸው አቅም የአጥቂ ክፍላቸውን ለማጠናከረ ለውጦችን በማድረግ ለማጥቃት ቢሞክሩም ጠንካራውን የወልዋሎ የተከላካይ መስመር መስበር ሳይችሉ ቀርተዋል። በ79ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ወደ ባህር ዳሮች የግብ ክልል ያመሩት ወልዋሎዎች በአፈወርቅ አማካኝነት ወርቃማ እድል ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በጨዋታው መገባደጃ ዳግም እንደ ጅማሮ የተቀዛቀዘው ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያስመለክት 0-0 ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡