የአሰልጣኞች አስተያየት | ደደቢት 2-3 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ዛሬ ከተደረጉ ጨዋታዎች ውስጥ አምስት ግቦች የታዩበት የደደቢት እና የቅዱስ ግዮርጊስ ጨዋታ ካለቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን አስየያየት ሰጥተዋል።

“ለዋንጫ ነው የምንጫወተው ብዬ መናገር አልችልም” ዘሪሁን ሸንገታ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ መጥፎ አይደለም በሁለታችንም በኩል የታየው። እነሱ መውረዳቸውን አውቀው ስለገቡ ከጫና ነፃ ሆነው ነበር የተጫወቱት። እኛም በልዩ ትኩረት በመጫወት ውጤቱን ይዘን ለመውጣት ነበር የገባነው።

ስለ ቡድናቸው የዋንጫ ተስፋ

ለዋንጫ ነው ምንጫወተው ብዬ መናገር አልችልም። ከፊታችን ያሉትን ጨዋታዎች አሸንፈን የተሻለ ደረጃዎችም ለማሻሻል እና የተጫዋቾቻችም ስነ-ልቦና ከፍ ለማድረግ ነው እየሰራን ያለነው። አምና እስከመጨረሻው ጫፍ ደርሰን ዋንጫውን አጥተናል። ዘንድሮ ሊሳካልንም ላይሳካልንም ይችላል፤ በቀጣይ ያሉንን ጨዋታዎች የተሻለ ነገር ሰርተን ተጫዋቾቻችን ወደ ጥሩ ነገር ማምጣት ላይ ነው እየሰራን ያለነው።

ስለ ስታድየሙ ድባብ

ስለ መቐለ ከተማ የእግር ኳስ ደጋፊ ምንም ማለት አልችልም። በጣም በጣም ጥሩ እና ጨዋ ነው ፤ እግር ኳስ እና እግር ኳስ ብቻ መሰረት ያደረገ በመሆኑ ሁሌም የማከብረው እና ደስ የሚለኝ ደጋፊ ነው። በዚ ቀጥሉ ነው የምለው።

“ይዘውት የወጡት ውጤት የሚገባቸው አይደለም” ዳንኤል ፀሐዬ

ስለ ጨዋታው

በጨዋታው መጀመርያ አከባቢ ጥሩ ነበርን ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ወርደን እስከ መጀመርያ አጋማሽ መገባደጃ ድረስ ብልጫ ተወስዶብናል።
ይህም ጎድቶናል። ከዕረፍት በፊት ነው ሁለት ግብ የተቆጠረብን ፤ ከዕረፍት በኃላ ግን የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገናል። በኳስ ቁጥጥር ረገድም የተሻልን ነበርን። ጨዋታው ተቆጣጥረነው ነበር።
ግብ ብናስቆጥርም ከዕረፍት በፊት በሰራናቸው ስህተቶች ምክንያት ውጤቱን መቀልበስ አልቻልንም። የዳኛው ውሳኔም ልክ አልነበረም። ሶስት ግዜ ዳኝቶን በተከታታይ ሁለት ተጫዋቾች በቀይ አስወጥቶብናል። ዛሬም ፍፁም ቅጣት ምቱ ለኛ ከልክሎ ነው ለነሱ የሰጣቸው። በሜዳህም እንዲህ በደል ሲደርስብህ በጣም ያበሳጫል።
ብንሸነፍም ብናሸነፍም ምንም አልነበረም፤ ያለቀ ጨዋታ ነበር ፍትሃዊ ጨዋታ ተጫውተን ባለመውጣታችን የራሱ የሆነ ነገር ነበረው።
ይዘውት የወጡት ውጤት የሚገባቸው አደለም።

ስለ ቡድኑ ቀጣይ እጣፈንታ

ስለሱ በዚ ሰዓት መናገር ከባድ ነው። በአስተዳደሩ ላይ ያሉት ሰዎች መልስ ቢሰጡበት የተሻለ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡