ከማል የእግር ኳስ አካዳሚ መልካም ተግባርን ፈፅሟል

በኢትዮጵያ እግር ኳስ አሻራቸውን ባኖሩት አሰልጣኝ ከማል አህመድ የተቋቋመው የከማል አካዳሚ ሙሉ ሰልጣኞች በተገኙበት በሀዋሳ መስጊድ የዒድ በዓልን አስመልክቶ ከ150 በላይ የሚሆኑ የተቸገሩ ወገኖችን መግቧል።

በሀዋሳ ከተማ ሁለት የፕሪምየር ሊግ እና አንድ የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ያነሱት የቀድሞው አሰልጣኝ ከማል አህመድ ምንም እንኳን በዕድሜ ምክንያት ከክለብ አሰልጣኝነት ቢገለሉም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ባቋቋሙት የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ አካዳሚ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከስልጠናው ባለፈ ለተቸገሩት ድጋፍን እያደረገ ያለው አካዳሚውም የፋሲካ በዓልን በማስመልከት ለክርስትና ዕምነት ተከታዮች ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን  በተመሳሳይ ዛሬ የእስልምና ዕምነት ተከታይ አቅመ ደካሞችን በመመገብ የበጎ አድራጎት ስራን ሰርተዋል፡፡ 

ይህን ያደረጉት በአካዳሚው ከሚሰለጥኑ ታዳጊዎች በተሰበሰበው ገንዘብ መሆኑን የገለፁት አሰልጣኝ ከማል ለወደፊቱም ቀጣይነት ባለው መልኩ በዚህ በጎ ተግባር ላይ እየተሳተፉ እንደሚዘልቁ ተናግረዋል። የአካዳሚው መስራች አሰልጣኝ ከማል ጨምረው እንዳሉት በአካዳሚዎች ደረጃ ይህን መሰል ተግባር ሲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ሌሎች አካዳሚዎችም ሆነ በክለብ ደረጃ ያሉት አካላት የበጎ አድራጎት ስራን እንዲፈፅሙ መክረዋል። የአካዳሚው ሰልጣኞችም ምንም እንኳን ተከፋይ ባይሆኑም በየስታድየሞቹ ወንድም ወንድሙን የሚፈነክትበት ደረጃ ላይ ለደረሰው የወቅቱ የተበላሸ የእግር ኳስ መንፈስን በጎ ገፅታም እንዳለው ለማሳየት እንዲሁም ለክለቦችም ጭምር ትምህርት በመስጠት ለተቸገሩ ወገኖች እርዳታ እንዲያደርጉ በማሳሰብ ተግባሩን መፈፀማቸውን ገልፀዋል፡፡

 

ላለፉት ሦስት ዓመታት ከ200 መቶ በላይ ሴት እና ወንድ ከ15 እና ከ13 ዓመት በታች ታዳጊዎችን አቅፎ እያሰለጠነ ያለውን ይኸው አካዳሚው ወደ ትልቅ ደረጃ ለማሳደግ  እንቅስቃሴ መጀመሩንም አሰልጣኝ ከማል አህመድ ለሶከር ኢትዮጵያ አያይዘው ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡