የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ ተጀመረ

ወደ 2012 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሚያልፉ ስድስት ቡድኖችን ለመለየት የሚደረገው የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ በባቱ ከተማ ተጀምሯል። በተደረጉ አራት ጨዋታዎችም ራያ፣ ቢሾፍቱ፣ አአ ፖሊስ እና ጋሞ ጨንቻ ድል አስመዝግበዋል።

የዛሬ ጨዋታዎችን በሁለት ሜዳዎች (ባቱ እና ሼር) ለማድረግ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ዛሬ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የባቱ ሜዳ ሙሉ ለሙሉ በውሃ የተሸፈነ በመሆኑ የዛሬ ጨዋታዎች በሙሉ በሼር ሜዳ እንዲካሄዱ ሆነዋል።

05:00 በምድብ ለ በተካሄደ የመጀመርያው የመክፈቻ ጨዋታ ራያ አዘቦን ከዳሞት ከተማ ሲያገናኝ ራያ አዘቦ በመጨረሻው ደቂቃ በተቆጠረች ወሳኝ ጎል 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፎ ሊወጣ ችሏል። ነፃ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ፣ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ የተፈጠረበት መልካም የሚባል ጨዋታ ሆኖ ባለፈው በዚህ ጨዋታ ራያ አዘቦዎች በጨዋታው የመጀመርያ አስር ደቂቃ ላይ ዳዊት አረፊ ሁለት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው የሚያስቆጩ ነበሩ። በተለይ ዳዊት የዳሞት ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ግብጠባቂውን ቅዱስ ዳኞን በማለፍ ኳስ እና መረብን ያገናኛል ተብሎ ሲጠበቅ ሳይጠቀምበት ወደ ውጭ የሰደዳት ኳስ የምታስቆጭ ነበረች።

ጥሩ የሜዳ ፉክክር እየተመለከትን በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 34ኛው ደቂቃ የዳሞቱ ግብጠባቂ ቅዱስ የሰራውን ስህተት ተከትሎ የራያው አጥቂ ጎይቶኦም ገ/ማርያም የውድድሩን የመጀመርያ ጎል አስቆጥሯል። ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማስቆጠር ብዙም ያልቆዩት ዳሞቶች 38ኛው ደቂቃ የራያ ተከላካዮች በፈጠሩት ስህተት የተገኘን ኳስ እሱባለው አንለይ የአቻነቱን ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ራያ አዘቦዎች በተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ ዳሞቶች ተዳክመው ነበር የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የቀረቡት። ያገኙትን ግልፅ አጋጣሚ በመጠቀም ረገድ ክፍተት የነበረባቸው ራያዎች በተለይ የፊት አጥቂዎቹ ዮሐንስ አድማሱ እና ጌታቸው ዘውዴ ያመከኗቸው ኳሶች የሚያስቆጭ ነበሩ። ከዳሞት በተሻለ መንቀሳቀሳቸው ጎል ማስቆጠር የሚገባቸው ራያዎች የማታ ማታ ጥረታቸው ተሳክቶ የጨዋታው መጠናቀቂያ በተቃረበበት ጊዜ 86ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሙሉ ካሕሳይ የዳሞትን ግብጠባቂ በማለፍ ተረጋግቶ ሁለተኛ ጣፋጭ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በማራኪ እንቅስቃሴ በራያ አዘቦ 2 –1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

07:00 በቀጠለው የምድብ ሀ ጨዋታ በቢሸፍቱ ከተማ እና ጎፋ ባሬንቼ መካከል የተደረገ ሲሆን በጨዋታውም ቢሸፍቱ ከተማ ከአንድ ዜሮ መመራት ተነስቶ 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ውድድሩን በድል ጀምሯል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የኦሜድላ ድንቅ ተጫዋች በነበረው በአሰልጣኝ ተስፋዬ ፈጠነ የሚሰለጥነው ጎፋ ባሬንቼ ተጭነው በተጫወቱበት ደቂቃ ውስጥ በ15ኛው ደቂቃ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ክብረወሰን እስራኤል ወደ ጎልነት በመቀየር ጎፋ ባሬንቼን መሪ ማድረግ ቻለ። በቀድሞ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እና የወንድ ፣ የሴቶችም ቡድን በማሰልጠን ስኬታማ በሆነው አሰልጣኝ አስራት አባተ የሚመሩት ቢሸፍቱዎች ጥሩ እግርኳስ መጫወት ቢችሉም ኳሳቸው እየተቆራረጠ በራሳቸው ላይ በሚፈጠር የመልሶ ማጥቃት አደጋ ቡድናቸው ሲቸገር የቆየ ቢሆንም የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር ቡድኑ ተረጋግቶ ቅርፅ እየያዘ በመምጣት ከእረፍት መልስ ተሻሽለው ቀርበው ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የአቻነት ጎል 55ኛው ደቂቃ በሚዛን አማን፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና በወልቂጤ በቅርብ ዓመታት ሲጫወት የምናቀው የቀኝ መስመር አጥቂው ሙሴ እንዳለ ከተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ኳስ ወደ ጎልነት ቀይሮ ቢሾፍቱን አንድ አቻ ማድረግ ችሏል።

ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ወስደው የተጫወቱት ቢሸፍቱዎች ብዙም ሳይቆይ በሀምበሪቾ ድንቅ የውድድር ጊዜ አሳልፎ ኢትዮጵያ ቡናን ከተቀላቀለ በኃላ ብዙም ሳይቆይ ከክለቡ ጋር ተለያይቶ ወደ አዲስ አበባ ከነማ ያመራው የአሁኑ የቢሸፍቱ አጥቂ ድንቅነህ ከበደ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የግብ ጠባቂውን አቋቋም በማየት ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ቢሸፍቱን መሪ አድርጓል። በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ እንደመውሰዳቸው ማሸነፍ የሚገባቸው ቢሸፍቱዎች ተቀይሮ በገባው አብዱልአዚዝ አማን የግንባር ኳስ ግሩም ሦስተኛ ጎል አስቆጥረው በ3-1 አሸናፊነት አጠናቀዋል።

09:00 በቀጠለው ሌላኛው ጨዋታ አዲስ አበባ ፖሊስን ከ ላስታ ላሊበላ አገናኝቶ አዲስ አበባ ፖሊሶች ባስቆጠሯቸው ሦስት ማራኪ ጎሎች ከመመራት ተነስተው 3-1 አሸንፈው ወጥተዋል።

በዛሬው ውሎ ላሊበላዎች ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩ ቢሆንም 25ኛው ደቂቃ ገዛኸኝ ፍቃዱ ከርቀት በመምታት ባስቆጠራት ምርጥ ጎል መሪ መሆን ችለው ነበር። ኳሱን አደራጅተው በመጫወት በፍጥነት ጎል ፍለጋ ሲንቀሳቀሱ የቆዩት አዲስ አበባ ፖሊሶች በ34ኛው ደቂቃ በኃይሉ አድሉ በእግራ እግሩ ከሳጥን ውጭ በመታት ግሩም ኳስ አቻ ሆነዋል። በወጣት አጥቂዎች የተዋቀረው የፖሊሶች የማጥቃት ኃይል ብዙም ጊዜ ሳይወስድባቸወረ የሰነዘሩት ጥቃት ተሳክቶላቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ከታዳጊ ቡድን እስከ ተስፋ ቡድን ሲጫወት የምናቀው ይስሐቅ ደረሰ እንደ ቡድን ጓደኛው ከርቀት ማራኪ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ከእረፍት መልስ ላስታዎች ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም ኳስና መረብን የሚያገናኝ አጥቂ አጥተው ሲቸገሩ የተመለከትን ሲሆን ይልቁንም የቡድኑን የመጫወት ፍላጎት ያወረደች ሦስተኛ ጎል በመልሶ ማጥቃት እዮብ ገ/ማርያም የተጣለለትን ኳስ ወደ ፊት ይዞ በመግባት 66ኛው ደቂቃ ለፖሊሶች ጎል አስቆጥሮ ላስታዎችን ተስፋ አስቆርጧል። በቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችሉ በርከት ያሉ የጎል እድሎችን ፖሊሶች መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ጨዋታው በአዲስ አበባ ፖሊሶች የበላይነት በ3-1 ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

11:00 ማምሻውን በተጀመረው የመጨረሻ ጨዋታ ጋሞ ጨንቻ በአስገራሚ እንቅስቃሴ የውድድሩ ጠንካራ ቡድን መሆኑን ባሳየበት አጨዋወት ቂርቆስ ክ/ከተማን 3-1 አሸንፎ ሊወጣ ችሏል። በጨዋታው ጅማሪ በፈጣን ማጥቃት በተደጋጋሚ የቂርቆስን በር በመፈተሽ መጫወት የቻሉት ጋሞዎች ያለቀለት የጎል እድሎችን ሲያመክኑ ቢቆዩም 13ኛው ደቂቃ በዕለቱ የጨዋታው ጅማሬ የጎል እድሎችን ሲያመክን ቆይቶ የነበረው የወደፊት ምርጥ አጥቂ እንደሚወጣው ያሳየው ማቲዮስ ኤልያስ ከግራ መስመር መሬት ለመሬት የተሻገረለትን ኳስ ወደ ጎልነት በመቀየር ጋሞዎችን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ። ተረጋግተው መጫወት ያቃታቸው ቂርቆሶች የሚደርስባቸውን ጫና መቆጣጠር ሲያቅታቸው አምሽተዋል። በተደራጀ እና በፍላጎት በመጫወት የተሻለ የሆኑት እና በወጣት የተገነባው የጋሞ ጨንቻ ቡድን ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ፍፁም ቅጣት ምት ማቲዮስ ኤልያስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በዚህ ሁሉ ሂደት ቂርቆሶችን አቻ ማድረግ የሚችሉ ግልፅ የጎል እድሎችን በማይታመን መልኩ ሄኒከን ዳምጠው አምክኗቸዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በቀጠለው ጨዋታ ማትያስ ኤርሚያስ ለራሱ ሁለተኛ እና ጋሞ ጨንቻን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል። ኳሱን ይዘው በመጫወት በጋሞ ጨንቻ ላይ የበላይነት የወሰዱት ቂርቆሶች ተቀይሮ በገባው አብዱልአዚዝ መሐመድ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ ችለው ነበር። ሆኖም የተወሰደባቸው ብልጫ ያሳሰባቸው ጋሞ ጨንቻዎች በፍጥነት የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጨዋታውን ተቆጣ ጥረው መጫወት ችለዋል። በተለይ ተቀይሮ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ መሐል ሜዳዉን በመቆጣጠር እና ወደ ፊት ለአጥቂዎች ነፃ ኳስ በማድረስ ወደ ፊት ተስፋ ያለው ተጫዋች መሆኑን ያሳየው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ሙሉዓለም መስፍን ታናሽ ወንድም የሆነው እንዳልካቸው መስፍን እንቅስቃሴ መልካም ነበር። በመጨረሻም የውድድሩ ክስተት እንደሆነ በብዙዎች የተነገረለት የጨንቻ ቡድን በበድሉ ሰለሞን ግሩም ሦስተኛ ጎል ታግዞ ጨዋታውን በአሳማኝ ሁኔታ 3–1 አሸንፎ ሊወጣ ችሏል።

የነገ ጨዋታዎች መርሐግብር

03:00 ሱሉልታ ከተማ ከ ቡሌ ሆራ

05:00
ባቱ ከተማ ከ ናኑ ሁርቡ

07:00
የጁ ፍሬ ወልዲያ ከ ሰሜንሸዋ ደብረ ብርሃን

09:00
መተሐራ ስኳር ከ ሶሎዳ አደዋ

( ሁሉም ጨዋታዎች በሼር ሜዳ ይደረጋሉ)


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡