የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24 ተሳታፊዎች እነማን ይሆናሉ ?

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሀያ አራት ቡድኖች መካከል ለሁለት ተከፍሎ እንደሚካሄድ ይፋ መሆኑ ይታወቃል። ፌዴሬሽኑ በውሳኔው እነማን እንደሚሳተፉ ባይገልፅም ከባለፈው የውድድር ዘመን ውጤት በመነሳት የሚሳተፉ ቡድኖችን እንመለከታለን።

ፕሪምየር ሊግ:– ከሊጉ የወረዱት ደቡብ ፖሊስ ፣ መከላከያ እና ደደቢትን በመመለስ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ (ሦስት ፎርፌን በመስጠቱ ከሊጉ የመሰናበት ዕጣ ቢኖረውም በድጋሚ ወደ ሊጉ በመመለስ) አስራ ስድስቱም ክለቦች ባሉበት ይቀጥላሉ። በተጨማሪም አዲስ አዳጊዎቹ ወልቂጤ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ሰበታ ከተማ ተካተው የተሳታፊዎቹ ቁጥር 19 ይሆናል።

ከፍተኛ ሊግ:- ከየምድቦቹ አሸናፊዎች በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ኢትዮጵያ መድን እና አርባ ምንጭ ከተማ ወደ ሊጉ ተቀላቅለው የሚሳተፉትን ቁጥር 22 ሲያደርስ በጥሩ ሦስተኛ የጨረሱት ኢኮስኮ (37 ነጥቦች) እና ነቀምት ከተማ (35 ነጥቦች) ወደ ሊጉ የሚቀላቀሉ ይሆናል።

በተያያዘም የቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በጥቅምት ወር መጨረሻ አልያም በኅዳር ወር ጅማሮ ላይ ሊጀመር እንደሚችልም ሰምተናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ