የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 0-1 ሩዋንዳ

በቻን ማጣርያ ኢትዮጵያ በሜዳዋ በሩዋንዳ መሸነፍፏ ይታወሳል። ከጨዋታው በኃላም የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።

“በህይወት ዕድል እንዳለ ሁሉ በእግርኳስም ዕድል አለ” ቪሴንት ሚሻሚ

ለተጋጣምያችን ትልቅ ክብር አለን። አንድ ቀሪ ጨዋታ ቢኖረንም ከጥሩ ቡድን ጋር ነው የተጫወትነው በቴክኒክም ፤ ታክቲክም የተቀናጁ ነበሩ። የዕድል ጉዳይ እንጂ ጥሩ ቡድን አላችሁ። ተጫዋቾቼን ማመስገን እፈልጋለው ፤ ኢትዮጵያን ማሸነፍ ቀላል ነገር አደለም።በጣም ደስተኞች ነን ፤ አንድ ደረጃ ከፍ ብለናል። መጥተው ጨዋታውን ለተከታተሉ ደጋፊዎችም አመሰግናለው።

ውጤቱ ይገባቹኃል ?

ለምን አይገባንም ? ጥሩ ተከላክለናል ዕድሎችም ፈጥረናል። በህይወት ዕድል እንዳለ ሁሉ በእግርኳስም ዕድል አለ።
ተጫዋቾቼ ጥሩ ተከላክለዋል በጣም ጠጣር ነበሩ። የስቴድየሙ ድባብ አላስቸገራቸውም። የስቴድየሙ ድባብም ጥሩ ነበር ደጋፊውን ማመስገን አለባችሁ።

“በመልሱ ጨዋታ ከዚህ በተሻለ ተንቀሳቅሰን ውጤት ይዘን ለመምጣት የተቻለንን እናደርጋለን።” አብርሃም መብራቱ

በጨዋታው ተጫዋቾቼ የሚችሉትን አድርገዋል። እንደተለመደው በግብ አካባቢ ስንደርስ መረጋጋት ባለመኖሩ ምክንያት የሳትናቸው ኳሶች ዋጋ አስከፍለውናል። እነርሱ ከቆመ ኳስ በተገኘ ዕድል ነው ግብ ያገቡብን። በቀጣይ ከቆመ ኳስ እኛ ላይ አደጋ የሚፈጥሩት ነገሮች ለማስተካከል ጠንክረን እንሰራለን። ያሉብንን የአጨራረስ ድክመቶችም አርመን በመልሱ ጨዋታ ከዚህ በተሻለ ተንቀሳቅሰን ውጤት ይዘን ለመምጣት የተቻለንን እናደርጋለን።

ስለ ሁለተኛው አጋማሽ ለውጥ

በመጀመርያው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በመከላከል ላይ ያመዘነ ጨዋታ ነበር የተከተሉት። እኛም ያንን ሰብሮ በመግባት የተፈጠሩት ዕድሎች መጠቀም ባለመቻላችን የተጫዋቾቻችን ሥነ ልቡና እንዲወርድ አድርጎታል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ክፍተታችን አርመን ብልጫ ወስደን ብዙ ሞክረን ነበር ፤ አልተሳካልንም። ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾችም ልዩነት ፈጥረዋል። በታክቲክ ያደረግነው ለውጥም ጥሩ ለውጥ አምጥቷል።

በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን ስለመቀልበስ

ብዙም ብልጫ ሳይወሰድብን በጥቃቅን ስህተት ነው ግቡ የተቆጠረብን። ከዚህ ውጪ ግን አስፈሪ የሚባል ነገር አልገጠመንም። በሥነ ልቡና ላይ እና ባሉብን ክፍተቶች ላይ ሰርተን የመልሱን ጨዋታ ለማሸነፍ እንዘጋጃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ