አዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ እንደማይፈርስ ተረጋገጠ

በ2011 የውድድር ዘመን ባጋጠመው የፋይናንስ እጥረት ምክንያት የመፍረስ አደጋ ውስጥ ገብቶ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ እንደማይፈርስ ታውቋል።

ክለቡ ከበጀት እጥረት ጋር ተያይዞ የመፍረስ አደጋ ውስጥ መግባቱን እና ከመፍረሱ አስቀድሞ የሚመለከታቸው አካላት ክለቡን እንዲታደጉ ሶከር ኢትዮጵያ በቀዳሚነት መዘገቧ ይታወቃል። አሁን የተሰማው መልካም ዜና የክለቡ የስራ አመራር ቦርድ አባል እና የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ጉዳዩ የከተማው ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ ጋር በዛሬው ዕለት እንዲደርስ ተደርጓል። ክቡር ከንቲባውም ለ2012 የውድድር ዘመን አስፈላጊው በጀት እንዲመደብ፣ በጠንካራ በባለሙያ የተደረገፈ የሥራ አመራር ቦርድ በፍጥነት እንዲዋቀር እና ክለቡ እንደ ክለብ በውድድር እንደሚቀጥል ማረጋገጫ በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ መመርያ ሰጥተዋል።

የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የከተማው ከንቲባ ላቀረቡት ጥያቄዎች ለሰጡት አፋጣኝ መልስ በክለቡ ስም አመስግነው በቅርቡ ክለቡን በአዲስ መልክ የማዋቀር ስራዎችን እንደሚጀምሩ ገልፀዋል።

በ2004 የተመሠረተው እና በ2008 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አድጎ የነበረው አዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ በሁለቱም ጾታዎች እና የተለያዩ የእድሜ እርከኖች እየተሳተፈ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ