የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 3-1 ሀዋሳ ከተማ

የአዳማ ከተማ ዋንጫ በዛሬው ዕለት ጅማሮውን ሲያደርግ በመክፈቻው ፋሲል በእሴይ ማዊሊ ሁለት እና በሙጂብ ቃሲም አንድ ጎል ሀዋሳ ከተማን 3-1 አሸንፏል። ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

” ጨዋታው ከወዲሁ ድክመት እና ጥንካሬያችንን እንድናውቅ ረድቶናል” ሥዩም ከበደ

ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ

አስቀድሞ ውድድሩ መዘጋጀቱ ለሁላችንም ቡድኖች የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ ነው። ምክንያቱም ከቅድመ ዝግጅት ነው ወደዚህ የመጣነው። ሊጉ ከመጀመሩ በፊት የቡድናችንን አቋም ለመለካት እንዲህ ያለ ውድድር ማግኘት በጣም ጥሩ ነው። ጨዋታው ለእኛ ጥሩ ነበር፤ ከወዲሁ ድክመት እና ጥንካሬያችንን እንድናውቅ ረድቶናል። በቀጣይ ጨዋታዎችም የቡድናችንን አቅም በደንብ እያየንበት እንሄዳለን።

አዲስ ስለተቀላቀሉ ተጫዋቾች

ቡድኑ ላይ ባሳለፍነው ዓመት በተለይ የተከላካይ አማካይ እና አጥቂ ላይ ክፍተት ነበር። የጋብርኤል አህመድ እና የኦሰይ ማውሊ መፈረም ለእኛ በእጅጉ ጠቅሞናል። ዛሬም ባለፈው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታም ያሳዩት እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነው። ሌሎቹም ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ተጨማሪ ጉልበት ይሆኑናል።

“ወጣቶችን በጨዋታው ላይ ለማየት ሞክረናል” አዲሴ ካሳ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። ከሰው ሰራሽ ሜዳ ዝግጅት ቆይታ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው በሳር ሜዳ ላይ ጨዋታ ያደረግነው። ያም ቢሆን እንቅስቃሴያችን መልካም ነው። ታዳጊ ወጣቶችን በጨዋታው ላይ ለማየት ሞክረናል። ከነባሮቹ ጋር እያቀናጀን ለሊጉ የምናደርገውን ዝግጅት እንቀጥላለን። በአጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነበር።

የቡድኑ የማጥቃት መንገድ

ያው ቅድም እንዳልኩት ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ነው ከአንድ ወር በላይ ስንዘጋጅ ቆይተን ዛሬ በሳር ሜዳ የተጫወትነው። ይህ ደግሞ የራሱ የሆነ ክፍተት አለው። ደጋግመን ወደ ጎል ደርሰናል። ሆኖም ውሳኔ ላይ ችግሮች ነበሩብን። እንዲህ ያሉ ውድድሮች መዘጋጀታቸውም ጠቀሜታቸው ክፍተትህን እንድታይ ነው። በቀጣይ ጨዋታዎች አስተካክለን እንመጣለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ