አአ ከተማ ዋንጫ| ባህርዳር ከተማ እና መከላከያ አቻ ተለያይተዋል

14ኛው የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ ሲቀጥል በምድብ አንድ ሁለተኛ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ከ መከላከያ አንድ አቻ ተለያይተዋል፡፡

ባህር ዳር ከተማዎች በመጀመሪያው ጨዋታ ከተጠቀሙበት የቡድን ስብስብ በርካታ ለውጦችን አድርገው ወደ ጨዋታው ሲገቡ በአንጻሩ መከላከያዎች ባሳለፍነው ሳምንት ጉዳት በገጠመው ፍሬው ሰለሞን ምትክ ተፈራ አንለይን ብቻ ቀይረው ወደ ጨዋታው ገብተዋል፡፡

ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሁለቱም ቡድኖች የግብ እድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ ባህርዳር ከተማዎች በ13ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ወርቁ ከመስመር ያቀበለውና ሲዲቤ ሞክሮ ወደ ውጭ ከወጣበት ኳስ ውጭ በመጀመሪያው አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራዎች አልነበሩም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከመጀመሪያው በተሻለ የመሸናነፍ ፉክክር ታይቶበታል፡፡ ማማዱ ሲዴቢ በ53ኛው ደቂቃ ከረጅም ርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ አክርሮ በመምታት ማራኪ ግብን በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ጥረት ያደረጉት መከላከያዎች ከሳጥን ውጭ በሚደረጉ ሙከራዎች ቤኒናዊውን የባህርዳር ግብ ጠባቂ ሲፈትኑ ተስተውለዋል፡፡ በስተመጨረሻም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ85ኛው ደቂቃ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በገባው አቤል ነጋሽ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ወሰኑ ዓሊ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የባህር ዳር ከተማው የፊት መስመር ተሰላፊ ማማዱ ሲዲቤ የጨዋታው ኮከብ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ