የደቡብ ሠላም የከፍተኛ ሊግ ውድድር ዛሬ ተጀመረ

በየዓመቱ የሚደረገው እና ዘንድሮም ለሶስተኛ ጊዜ የሚከናወነው የደቡብ ሠላም የከፍተኛ ሊግ ክለቦች የአቋም መፈተሻ ውድድር ዛሬ በሀላባ ከተማ አዘጋጅነት ተጀምሯል፡፡ 

ውድድሩን ቀደም ብሎ በስድስት ቡድኖች መካከል ለማድረግ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ትላንት ለሶከር ኢትዮጵያ ቢገልፅም ክለቦች በበጀት እጥረት ምክንያት በውድድሩ እንደማይሳተፉ በመግለፃቸው አራት ክለቦች ብቻ የሚሳተፉ ይሆናል። ሁሉም ቡድኖች እርስ በእርስ ጨዋታ ካደረጉ በኋላ በነጥብ ብልጫ አሸናፊው የሚለይበት እንዲሆን ዛሬ ረፋድ ፌድሬሽኑ ወስኗል፡፡

ሀላባ ከተማ፣ ቡታጅራ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ከከፍተኛ ሊጉ ሲሳተፉ ጂንካ ከተማ ደግሞ ከአንደኛ ሊግ በውድድሩ ላይ ተወዳዳሪ የሆኑ ክለቦች ናቸው፡፡

የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ ብሩክ ቡናሮ እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ደመላሽ ይትባረክ በክብር እንግድነት በተገኙበት የዛሬው የሀላባ ከተማ እና ቡታጅራ ከተማ የመክፈቻ ጨወዋ ሀላባ ከተማ የመስመር አጥቂው አቡሽ ደርቤ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1ለ0 አሸንፏል፡፡ ውድድሩ ነገም ሲቀጥል ሀምበሪቾ ዱራሜ ጂንካ ከተማን ይገጥማል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ