አዲስ አበባ ከተማ ከዋና አሰልጣኙ ጋር ሲቀጥል ለሴት ቡድኑ አሰልጣኝ ሾሟል

አዲስ አበባ ከተማ አሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሀንስን በወንዶች ቡድን አሰልጣኝነት እንዲቀጥሉ ሲወሰን ሙሉጎጃም እንዳለን የሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሁለቱም ፆታ እንዲሁም በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ተሳታፊ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በቅርቡ ይፈርሳል እየተባለ ቢገለፅም ኋላ ላይ ግን ክለቡ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ክለቡ መቀጠሉ ከተረጋገጠ በኋላ ለሁለቱም ቡድኖች የአሰልጣኝ ቅጥር ማስታወቂያን በማውጣት ለመቅጠር ያሰበ ቢሆንም ትላንት ክለቡ ባደረገው ስብሰባ ይህን ሀሳብ በመተው በክለቡ የነበሩትን አሰልጣኞች ለማስቀጠል ወስኗል፡፡

በዚህም መሠረት የወንድ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት በ2011 ሲመሩ የነበሩት አሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ የአንድ ዓመት ቀሪ የውል ጊዜ ስለነበራቸው ወደ ስራ ገበታቸው ተመልሰው እንዲሰሩ የተደረገ ሲሆን ክለቡ አይቀጥልም መባሉን ተከትሎ ብዙ ተጫዋቾችን በመልቀቁ አሰልጣኙ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል። በቅርቡም ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡

ክለቡ ለሴቶች ቡድኑ ዐምና በረዳት አሰልጣኝነት ስትሰራ የነበረችነውና ከአሰልጣኝ መሠረት ማኒ ጋር ከተለያዩ በኋላ በሉለተኛው ዙር በርካታ ጨዋታዎችን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ስትመራ የቆየችው ሙሉጎጃም እንዳለን በቋሚነት አሰልጣኝ በማድረግ ሾሟል፡፡ አሰልጣኟ ከዚህ ቀደም በከማል አህመድ ማሰልጠኛ እና በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ውስጥ በመስራት ያሳለፈች ሲሆን በተጫዋቾችነት ዘመኗም ለብሔራዊ ቡድን ተሰልፋ መጫወት ችላለች። እንደ ወንዶቹ ሁሉ በርካታ ተጫዋቾችን ያጣው የሴቶች ቡድኑ በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ይፈፅማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተያያዘ ክለቡን በሥራ አስኪያጅነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ወደ ቀድሞ ክለባቸው ኢትዮጵያ ቡና በማምራታቸው ክለቡ በቅርቡ አዲስ ሥራ አስኪያጅ በቦታው ተክቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ