የሽረ ስታዲየም እድሳት የመጨረሻው ምዕራፍ ደርሷል

የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ስሑል ሸረ የሚጫወትበት የሽረ እንዳሥላሴ ስታዲየም በሁለተኛው ዙር ግልጋሎት መስጠት ይጀምራል።

ላለፉት ወራት በእድሳት የቆየው የሽረ እንዳስላሴው ስታድየም የሳር ተከላ ሂደቱ ተጠናቆ ግልጋሎት ለመስጠት በመዘጋጀት ይገኛል። ጉዳዩን አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ቆይታ ያደረጉት የስሑል ሽረ ሥራ አስከያጅ አቶ ተስፋይ ዓለም የስቴድየሙ እድሳት በመጠናቀቅ እንደሚገኝና በሁለተኛው ዙር ቡድናቸው ወደ ሜዳው እንደሚመለስ ገልፀዋል።

“የሳር ተከላ ሥራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፤ ስታዲየሙ ከአንድ ወር ከአስር አምስት ቀናት በኃላ ሥራውን ይጀምራል ብለን ነው የምንጠብቀው ” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ተስፋይ ዓለም ቡድናቸው በቅርቡ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ገልፀዋል” በሀሳብ ደረጃ የመጀመርያው ዙር ከመጠናቀቁ በፊት ለመመለስ ነው ያቀድነው። ግን ሳሩ ሁለት ግዜ መታጨድ ስላለበት ሂደቱን በጠበቀ መንገድ ሁለተኛውን ዙር በሜዳችን መጫወት እንጀምራለን።” ብለዋል።

በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ስሑል ሽረ የሜዳው ጨዋታዎቹን በመቐለው ትግራይ ስታዲየም እያካሄደ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ነገ በ9ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማን ያስተናግዳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ