ሪፖርት| የዳዊት እስጢፋኖስ ግሩም የቅጣት ምት ግቦች ሰበታን ከወልዋሎ ነጥብ እንዲጋራ አስችለዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዓዲግራት ላይ ወልዋሎ ከሰበታ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። ወልዋሎ በተከታታይ ጨዋታ የሁለት የግብ ልዩነት መሪነት አሳልፎ ሲሰጥ ዳዊት እስጢፋኖስ ሰበታን ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ ረድቷል።

በጨዋታው ወልዋሎዎች ከባለፈው ሳምንት አሰላለፋቸው ዓይናለም ኃይለ፣ ሄኖክ መርሹ፣ ፍቃዱ ደነቀ እና ጠዐመ ወልደኪሮስን በማሳረፍ አሞስ አቼምፖንግ እና በአዲስ ፈራሚዎቹ ያሬድ ብርሀኑ፣ አመለ ሚልክያስና ዮናስ በርታ ተክተው ገብተዋል። እንግዶቹ ሰበታዎችም ከባለፈው ሳምንት ስብስብ ዳንኤል አጄይ፣ ኢብራሂም ከድር፣ ፍርዳወቅ ሲሳይ እና ሳሙኤል ታዬ በፋሲል ገብረሚካኤል፣ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ አስቻለው ግርማ እና ጌቱ ኃይለማርያም ተክተው ገብተዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው እና ማራኪ እንቅስቃሴ ባልታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተሻሉ የነበሩበት፤ ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎችም በርካታ የግብ ሙከራዎች ያደረጉበት ነበር።

በጨዋታው ቀጥተኛ እና የመስመር አጨዋወቶች የተገበሩት ወልዋሎዎች ምንም እንኳ በተጋጣሚያቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ሙከራ በማድረግ ረገድ ግን የተሻሉ ነበሩ። ካደረጓቸው ሙከራዎችም ዐመለ ሚልክያስ መቷት ፋሲል ገብረሚካኤል ያዳናት ሙከራ እና ጁንያስ ናንጂቡ ከኢታሙና ኬይሙኔ የተሻገረችለት ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው እንደምንም ያዳናት ኳስ ይጠቀሳሉ።

በአጋማሹ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ደርሰው ግብ ሙከራ ለማድረግ ያልሰነፉት ወልዋሎዎች በአስራ ስምንተኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ጁኒያስ ናንጂቡ ያሬድ ብርሀኑ ያቀበለውን ኳስ ተጫዋች አልፎ ተረጋቶ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው።

ጁንያስ ናንጂቡ ከግቧ በኃላም ብዙ ሳይቆይ ሁለተኛ ግብ የማስቆጠር ዕድል አግኝቶ አባክኗል። አጥቂው ያሬድ ብርሀኑ በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ግብ ጠባቂውን አታሎ ነበር ንፁብ ግብ ያመከነው።

በአጋማሹ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሰበታዎች በአጨዋወቱ የግብ ዕድሎች ፈጥረው ኢላማው የጠበቀ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ሆኖም በናትናኤል ጋንቹላ በሁለት አጋጣሚዎች የተደረጉ ሙከራዎች እና ፍፁም ዳዊት አቀብሎት በውሳኔ አሰጣጥ ድክመት ያባከናት ንፁህ ዕድል ይጠቀሳሉ።

በቁጥር እጅግ ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የታየበት ሁለተኛ አጋማሽ እንደተጀመረ የተጋጣሚን ግብ መፈተሽ የጀመሩት ቢጫ ለባሾቹ በአርባ ስምንተኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በናሚቢያዊው አጥቂ ኢታሙና ኬሙይኔ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። አጥቂው ሳሙኤል ዮሐንስ አክርሮ መቷት ወጣቱ ግብ ጠባቂ የተፋትን ኳስ አግኝቶ በማስቆጠር ነበር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረገው።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ ሁለት ቅያሬዎች ያደረጉት ሰበታዎች በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ዕድሎች ባይፈጥሩም በዳዊት እስጢፋኖስ የቅጣት ምት ብቃት ሁለት ግቦች አስቆጥረው ከመመራት ተነስተው ነጥብ ተጋርተዋል። አማካዩ በስልሳ ሦስተኛው ደቂቃ በድንቅ የቅጣት ምት የግብ ልዩነቱን ሲያጠብ ዘጠና ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃም ከመሀል ሜዳ በተመሳሳይ መንገድ ከቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑ አንድ ነጥብ ተካፍሎ እንዲወጣ አስችሏል።

ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የወልዋሎ ደጋፊዎች በክለቡ አመራሮች ላይ የከረረ ተቃውሞ አሰምተዋል። በጨዋታው ደካማ ብቃት ያሳየው እና ብቃቱ ወርዷል ተብሎ ቅሬታ ሲገጥመው የቆየው ጊኒያዊው ግብጠባቂ ዓብዱልዓዚዝ ኬይታም ሌላው የከረረ ተቃውሞ የገጠመው ተጫዋች ነው።

©ሶከር ኢትዮጵያ