“ሐት-ትሪክ የሰሩት እግሮች” ትውስታ በዳዊት መብራቱ (ገዳዳው) አንደበት

ትውልድና እድገቱ አዲስ አበባ ኦሎምፒያ አካባቢ ልዩ ስሙ 35 ሜዳ ነው። በአየር መንገድ በታዳጊ (C) ቡድን ታቅፎ በፍጥነት ወደ ዋናው ቡድን ያደገ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ከስባት ያልበለጠ ጨዋታ አድርጎ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ “ገዳዳው” የሚለውን ቅፅል ስም በመያዝ ከአየር መንገድ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተቀላቀለው። ከስሙ በላይ መለያው (መጠሪያው) የሆነውን ገዳዳው የሚለውን ቅፅል ስም ያወጣለት በወቅቱ በአየር መንገድ አብሮት ይጫወት የነበረውና አሁን የኢትዮጵያ ቡና ምክትል አሰልጣኝ የሆነው ዘላዓለም ፀጋዬ ነው።
በግሉ የኮከብ ተጫዋችነት ክብር አያገኝ እንጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘጠናዎቹ ውስጥ ለተቀናጃቸው ታላላቅ ዋንጫዎች የእርሱ ድርሻ ከፍተኛ ነው። በእሱ ዘመን ከተጫወቱ የመስመር ተጫዋቾች ተስተካካይ የሌለው እንደነበረም ብዙዎች ይስማሙበታል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስምንት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በማንሳት ስኬታማ የሆኑ አስር ዓመታት ቆይታ ካደረገ በኋላ እግርኳስ እስካቆመበት ጊዜ ድረስ ለሰበታ ከተማ የተጫወተው ዳዊት በ1998 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ አንደኛ ዙር ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም የጋናው ታላቅ ክለብ ኸርትስ ኦፍ ኦክን 4-0 በረታበት ጨዋታ ሐት-ትሪክ የሰራበት ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ የሚታወስ ነው። በኢትዮጵያ እግርኳስ የክለቦች ታሪክም በአፍሪካ መድረክ ከአሰግድ ተስፋዬ (5) በኋላ በአንድ ጨዋታ ሦስት ጎል ያገባ ተጫዋች መሆን ችሏል።

ከኢትዮጵያ ከወጣ ቆየት ያለው ዳዊት ከሚኖርበት ሀገረ አሜሪካ ሐት-ትሪክ ስለሰራበት አጋጣሚና ስለ በመልሱ ጨዋታ ስለተፈጠረው ክስተት በትውስታ አምዳችን ይሄን ነግሮናል።

“በመጀመርያ እኔን ለቃለ መጠይቅ መርጣቹሁ ስላቀረባችሁኝ ከልብ አመሰግናለው። ተጋጣሚያችን ኸርትስ ኦፍ ኦክ ትልቅ ቡድን ነው። የመጀመርያውን ጨዋታ እኛ ሜዳ በመሆኑ የግድ እዚሁ ጨዋታውን ጨርሰን መሄድ እንዳለብን ተነጋግረን በደንብ ነበር የተዘጋጀነው። ለዛ ነበር በጥሩ ውጤት እኔም ሐት-ትሪክ እንድሰራ ምክንያት የሆነው። በወቅቱ በነበረው ነገርም በጣም ደስተኛ ነኝ። ጋና ላይ የነበረው የመልሱ ጨዋታ ግን በጣም የሚያሳዝን ነበር። ምንም ህግ የሌለበት፣ የደረሰብንን የምንነግረው ያጣንበት፣ ገና ሜዳ ሳንገባ ጫማችንን የተወሰደበት… ብቻ እጅግ የሚያሳዝን በደል ነበር የተፈፀመብን። የዕለቱ ዳኛ ጨዋታውን በመጀመርያው አርባ አምስት እንዲያልቅ እንደፈለገ ያስታውቅ ነበር። ወደ ሰባት ተጫዋቾችን ቢጫ ማስጠንቀቂያ አሳይቷል፤ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቶብናል። አንድ ደሞ አስራ ስድስት ከሀምሳ ውስጥ ቅጣት ሰጥቷል። በጣም የሚገርመው የዳኛው ዓይን ያወጣ በደል 45+2ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጥ ሲል በቃ ጨዋታው ተበጠበጠ፤ እኛም አቋርጠን ወጥተን ወደ ሀገራችን ተመልሰናል።”

በቀጣይ አይረሴ የሆኑ የዳዊት “ገዳዳው” ሌሎች ትውስታዎችን የምናቀርብ ይሆናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ