“እቅዶቼን ለማሳካት ጠንክሬ እሰራለሁ” ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ምንተስኖት ጊንቦ

ታዳጊዎችን በማፍራቱ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሰው የሀዋሳ ታዳጊ ቡድን ተገኝቶ በሁለት የወጣት ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ ለሀገሩ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ በፍጥነት እድገቱን እያጎለበተ የመጣው እና ወደ ፊት እንደ ችግር የሚታየውን የግብ ጠባቂዎች ችግር ይቀርፋል እየተባለ የሚነገርለትና ዓምና ወደ ሀዋሳ ዋናው ቡድን ያደገው ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ምንተስኖት ጊንቦ የዛሬው የተስፈኛ አምድ ተጋባዥ ነው፡፡

በተለምዶ 07 እየተባለ በሚጠራው በአንዱ የሀዋሳ ሰፈር ውስጥ ነው ተወልዶ ያደገው ቤኒያሚን እየተባለ የሚጠራው የአካባቢው ሜዳ ደግሞ ኳስ ተጫዋች ለመሆኑ ቁልፍ መሠረት ያስያዘው ቦታ ነበር፡፡ ብሩህ ተስፋ በሚባል የፕሮጀክት ቡድን እግር ኳስን ጀመረ 2009 ለሀዋሳ ከተማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ተመልምሎ በፕሪምየር ሊጉ ደረጃ ለመጫወት በቅቷል፡፡ በዛኑ ዓመት ከሀዋሳ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እና የጥሎ ማለፉን ደርቦም አንስቷል፡፡ ባሳየውም ጥሩ አቋም ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ተመርጦ ብሩንዲ በነበረው የ2009 የሴካፋ ቡድን ሀገሩን አገልግሏል፡፡

2010 በሀዋሳ ከ20 አመት በታች ቡድን በመጫወት ካሳለፈ በኃላ ዓምና በድጋሚ ሀገሩን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጦ መጫወት ችሏል፡፡ ዩጋንዳ በነበረው ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫ ላይ ማለት ነው፡፡ የ2009 የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመባል የተሸለመው እና አምና ወደ ሀዋሳ ከነማ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ምንተስኖት ጊንቦ በዛሬው የተስፈኛ አምዳችን ስለ እግርኳስ ሕይወቱ አውግቶናል፡፡

“ኳስን የጀመርኩት በሰፈሬ ባለው ቤኒያሚን ሜዳ ብሩህ ተስፋ በሚባል ቡድን በአሰልጣኝ ሳሚ ፕሮጀክት ውስጥ በመስራት እና በመጫወት ነው በዛ ጊዜም በሀዋሳ በሚደረጉ የውስጥ የታዳጊ ውድድሮች ላይ ተጫውቼ አሳሌፌያለሁ በግሌም ለመጫወት ካለኝ ፍላጎት ወደ ሌላ ሀገሮች እየወጣውም እጫወት ነበር፡፡

“በብሩህ ተስፋ ፕሮጀክት እየተጫወትኩ 2009 ለሀዋሳ የታዳጊዎች ምልመላ አለ ሲባል ተስፋዬ ወደሚባል ፕሮጀክት ሄጄ መጫወት ጀመርኩ። እዚህ ቡድን ውስጥ እያለሁ ነበረ ሙከራ ያደረኩት ግብ ጠባቂዎች ለብቻ ነበር በምልመላው ወቅት ሲታዩ የነበረው። ያንን ምልመላ አልፌ የሀዋሳ ከ17 አመት በታች የታዳጊዎች ቡድን አሰልጣኝ ብርሀኑ (ፈየራ) ተመልክቶኝ ወደ ቡድኑ አስገባኝ፡፡

“ዕድሉን ያገኘሁት 2009 በገባሁበት ዓመት ነበር። ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ተሳታፊ ነበር። ሀዋሳ ከተማ ዕድለኛም ሆኜ ሁለት ዋንጫን የፕሪምየር ሊጉንም ሆነ ጥሎ ማለፉን ጨምሮ አግኝቻለሁ። በሰዓቱ ባሳየውትም እንቅስቃሴ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብዬ ተመርጫለሁ። ከዛ በኃላ ሳልጠብቀው በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና አማካኝነት ብሩንዲ በነበረው የሴካፋ ዋንጫ ተመርጪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን አገልግያለሁ።

“ከ17 ዓመት በታች የሀዋሳ ቡድን 2010 ላይ ወደ ላይ አደኩኝ። ማለትም ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በፕሪምየር ሊጉም እስከ ማጠቃለያ ውድድር ድረስ ተጫውቻለሁ። አሁንም ጥሩ ነገር በማሳየቴ ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ 2011 ዓምና ተጠርቼ ዩጋንዳ ላይ በነበረው ጨዋታ ተሳትፌያለሁ።

“ለሀገር ተመርጦ መጫወት በጣም ደስ ይላል፤ ከዚህ በላይ የሚያረካ ነገር የለም። ለሀገር መጫወት አደራው እና ስሜቱ ከባድ ስለሆነ ሁለት ጊዜ ስመረጥ በሰዓቱ ልዩ ስሜት ነበር የተሰማኝ እና በጣም ደስ ይላል።

“ሀዋሳ ከነማ እንደሚታወቀው ብዙ ዋንጫዎችን ያነሳ ቡድን ነው። የፕሪምየር ሊግ ዋንጫንም አንስቷል፡፡ እዚህ ቡድን ውስጥ ተካትቼ ወደ ዋናው ቡድን ማደጌ ልናገር ከምችለው በላይ ነው ደስታ የተሰማኝ፤ ካደኩኝ ገና አንድ ዓመቴ ነው። ከፈጣሪ ጋር ዋናው ቡድን ላይ አንደኛ ሆኜ ለመጫወት የቻልኩትን እና የሚጠበቅብኝን አደርጋለሁ። ፈጣሪ ይርዳኝ ይሆናል ብዬ ደግሞ አስባለሁ።

“እንደማንኛውም ተጫዋች በውጪ የመጫወት ዕቅድ አለኝ። ከሀዋሳ ጋር ዋንጫን ማንሳትም እፈልጋለሁ። ዋና አላማዬ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ነው። ሲቀጥል ደግሞ በታዳጊ ብሔራዊ የጀመርኩትን በዋናው ብሔራዊ ቡድን ቀጥዬ ሀገሬን ትልቅ ደረጃ ማድረስም እፈልጋለሁ። ይህን ለማድረግ ግን ጠንክሬ እሰራለሁ እዛ ለመድረስ።

“ተጫዋች እንድሆን በእኔ ህይወት ብዙ ሰዎች አስተዋጽኦ አላቸው ማመስገን የምፈልገው። በአንደኝነት አጎቴ ተጫነ ረዳን ኳስን ስጀምር አይዞህ እያለ እያበረታታኝ ትልቁ ደረጃ ይወስዳል። ሲቀጥል ሀዋሳ ከነማ ታዳጊ ቡድን ያሰለጠነኝ ብርሀኑ ፈየራ በጣም በጣም ማመስገን ምፈልገው ትልቅ አሰልጣኝ ነው፡፡ ተመስገን ዳናም በብሔራዊ ቡድን እንድጫወት የረዳኝ ነው በተመረጥኩኝ ሰዓት ደግሞ የበረኛ አሰልጣኝ የነበረው በለጠ ወዳጆም ጥሩ ነገር ለኔ ነበረው። ላመሰግናቸው ወዳለሁ፤ በእኔ ህይወት ትልቅ አስተዋፅኦ ላላቸው ሁሉንም አመሰግናለሁ”፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: