ስለ ስምዖን ዓባይ ሊያውቋቸው የሚገቡ ዕውነታዎች

ለሀገሪቱ ትላልቅ ቡድኖች መጫወት ችሏል። ተከላካዮች አታሎ የማለፍ ብቃቱ፣ በፍጥነት የሚወስናቸው ውሳኔዎች እና ጎል ለማስቆጠር የነበረው ዕይታ የተለየ ነው። የታሪካዊው ቤተስብ ፍሬ፣ የዓባይ ጌታሁን ልጅ እና የዮርዳኖስ ዓባይ ታላቅ ወንድም ነው። ይህ የዘጠናዎቹ ድንቅ አጥቂ ስምዖን ዓባይ ማነው ?

ወቅቱ 1993 ነው። በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መብራት ኃይል ከሙገር ሲሚንቶ ጋር ጨዋታ ያደርጉና መብራት ኃይል 5-0 በሆነ ውጤት ያሸንፋል። ታዲያ በወቅቱ የነበረው ካንቦሎጆ የተሰኘ የህትመት ጋዜጣ ጨዋታውን እንዲህ ሲል ገልፆታል ” ዓባይ ሙገርን አጥለቀለቀው!” ይህን ማለቱ ዮርዳኖስ ዓባይ ሦስት ፣ ስምዖን ዓባይ ሁለት ጎል በድምሩ የተገኘውን አምስት ጎል በስማቸው ያስመዘገቡት የዓባይ ቤተሰቦች (ልጆች) በመሆናቸው ነው።

እነዚህን ምርጥ የኢትዮጵያ እግርኳስ ከዋክብት ያስገኙት ጋሽ ዓባይ ጌታሁን ደግሞ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ሐረር ምርጥ እና ድሬደዋ ጥጥ ማኀበር (ጨርቃ ጨርቅ) ተጫውተው ያሳለፉ ምርጥ ተጫዋች ነበሩ። በእርሳቸው ያላበቃው የእግርኳስ ተጫዋችነት ሱሱ በልጆቻቸው ተጋብቶ ቀጥሏል። የዛሬ ባለተራ እንግዳችን ስምዖን ዓባይ ድሬዳዋ ከተማ ልዩ ስሟ ደጃቱ በተባለች መንደር ከቤታቸው አስር ሜትር ቀረብ ብላ በምትገኘው አሸዋ ሜዳ እግርኳስን መጫወት ጀምሯል። እድሜው ከፍ ሲል በ1984 በድሬደዋ ጨርቃጨርቅ “C” ቡድን ውስጥ አባል ሆኗል። ብዙም ሳይቆይ ወደ “B” ቡድን አድጎ ተጫውቷል። በወቅቱ የድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ዋናው ቡድን አባላት የነበሩ ሰባት ሰዎችም በተላላፊ በሽታ በመጠቃታቸውን ተከትሎ ስምዖን ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ችሏል።

በአንድ አጋጣሚ በልምምድ ወቅት በጨርቃጨርቅ ዋናው ቡድን ውስጥ ተሾመ የሚባል ነባር ተከላካይ ተጫዋች ነበር። ሁሌም ማንም አያልፈኝም በማለት የሚናገር ነው። ታዲያ በዕድሜም፣ በሰውነት ትንሹ የነበረው ስምዖን በግሩም ሁኔታ አልፎት ጎል ያስቆጥራል። ተሾመ ይህን ነገር አላመነም ጫማዬ አሸራቶኝ ነው በማለት በቀጣይ የልምምድ ቀን ገዝቶ ያስቀመጠውን አዲስ ጫማ ተጫምቶ ይመጣል። “ስምዖን ደግሞ አብዶ ሰርቶ ሲያልፈው አንተ ላሽ (እንሽላሊት) ነህ” በማት እግርኳስን ማቆም አለብኝ ብሎ በማመን እንደወሰነ በጊዜው የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ።

በዋናው ቡድን በመጀመርያው ጨዋታው ጎል በማስቆጠር አሰልጣኝ ጌታቸው ወልዴን አሳምኖ በዛው ቡድን ውስጥ እንዲቆይ የተደረገው ስምዖን ለሦስት ዓመታት በጨርቃጨርቅ ቆይታ ካደረገ በኃላ በአሰልጣኝ ወርቁ ደርገባ ጥሪ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫውቷል።

ቀጠን ያለ ቢሆንም ፈጣን፣ ሰውነቱን እንደፈለገ ማዘዝ እንደሚችል የሚነገርለት ስምዖን ከንግድ ባንክ በኃላ ለአንድ አንድ ዓመት ያህል መድን እና ኢትዮጵያ ቡና ከተጫወተ በኃላ ኢትዮ ኤሌክትሪክ መድገም ያልቻለውን ብቸኛውን የሦስትዮሽ ድል ያሳካበትን የ1993 ቡድንን በመቀላቀል ከታናሽ ወንድሙ ዮርዳኖስ ዓባይ ጋር የፊት መስመሩን በጥምረት በመምራት አስደናቂ ቆይታ አድርጓል።

ታላቅ ወንድሙ ምን ዓይነት ተጫዋች እንደነበረ ልዩነት ፈጣሪውን አጥቂ ዮርዳኖስ ዓባይ ይሄን መስክርነት ይሰጣል። ” ስምዖንን ከኔ በላይ ብዙዎች ይገልፁታል፤ እኔ እንዳውም በደንብ ላልገልፀው እችላለው። መብራት ኃይል እና በትንሹ ቡና አብረን ለመጫወት ነው የተገናኘነው። ስምዖን አጥቂ ላይ እኔ የምወድለት ነገር ቶሎ ቢኖር ብሎ የሚወስናቸው ነገሮች በጣም ፈጣን ናቸው። አዕምሮውን እና እግሩን ቶሎ አገናኝቶ የሚያደርገው ነገ ደስ ይለኛል። በእግርኳስ ችሎታውም በጣም አሪፍ የሆነ ተጫዋች ነበር።” ይለዋል።

ስምዖን በመብራት ኃይል ሦስት ዓመት ከቆየ በኃላ ዳግመኛ ለአንድ ዓመት ኢትዮጵያ ቡና ተጫውቶ በ1996 ጫማውን ሊሰቅል ችሏል። በኢትዮጵያ ታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ መጫወት የቻለው ስምዖን በተለይ በ1987 ኬንያ ላይ በተካሄደው የታዳጊዎች የሴካፋ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ሀገሩን ባለ ድል ከማድረጉ በተጨማሪ በግሉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቁ ይታወሳል።
በድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ አብሮት የተጫወተው እና ስምዖን እንደቤተስብ እንደ ወንድም እና አባት የሚቆጥረው የቀድሞ ተጫዋች አበበ ኃይሉ ስለ ስምዖን እንዲህ ይናገራል “የአጨራረስ ብቃቱ ጥሩ የሆነ፣ ኳሱን በእግሩ ከያዘ ሽባ አድርጎህ አልፎ የሚሄድ። አንድ ሰው ካገኘ ለእርሱ ቀላል ነው። ማንም ይሁን ማን ገድሎህ ነው የሚሄደው። ሁለት ሰው ካገኘ በደብል ፓስ አልፎ የሚሄድ፣ በሁለት እግሩ መጫወት የሚችል። አዕምሮው ከባድ የሆነ ተጫዋች ነበር።” በማለት ይገልፀዋል።

እግርኳስን በማቆም በኃላ ብዙም ሳይቆይ ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ በመቀላቀል በ1997 ተስፋ ለኢትዮጵያ በተባለው ቡድን የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ምክትል በመሆን የአሰልጣኝነት ህይወቱን ጀምሯል። በተለያዩ ዓመታት የድሬዳዋ ተስፋ መብራት ኃይል ቅርጫፍ የታዳጊ ፕሮጀክት፣ የናሽናል ሲሚንት እና ድሬደዋ ፖሊስ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ሲያገለግል ቆይቶ ከ2009 ጀምሮ የድሬደዋ ከነማ ዋናው ቡድን ከተለያዩ አሰልጣኞች ጋር በምክትል አሰልጣኝነት ቢሰራም በመሐል በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ሲያሰለጥን ቆይቷል። ከ2011 አጋማሽ ድረስ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝነት በመሆን አገልግሏል። በዘጠናዎቹ ከነበሩ ስመ-ጥር አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው የዛሬው ዕንግዳችን ስምዖን ዓባይ በተጫዋችነት እና የአሰልጣኝነት ቆየበት የ27 ዓመት የእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ጥሩ ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ!

“በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ ለኔ ስኬት የምለው በድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ የድሬዳዋ ሻምፒዮና እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን አግኝቻለው። ድሮ የየየክፍለ ሀገሩ ምርጦች የሚካፈሉበት ግንቦት 20 የሚባል ውድድር ነበር። እሱን ከድሬዳዋ ምርጥ ጋር ዋንጫ አግኝቻለው፤ የውድድሩ ምርጥ ተጫዋችም ሆኛለው። ለእኔ ግን በጣም የሚያስደስተኝ ስኬት 1987 ላይ በኬንያ በታዳጊዎች የምስራቅ አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ እኔ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ መድን ይጫወት የነበረው በላይ ደግሞ ኮከብ ተጫዋች የነበረበት እና ዋንጫውንም ያነሳንበት ጊዜ ነው። ሌላው ደግሞ 1993 በመብራት ኃይል ወንድሜም የኮከብ ግብ አግቢ የነበረበት እና የሊጉን ዋንጫም ያነሳንበት ነበር። እነዚህ ናቸው በጣም የሚያስደስቱኝ ስኬቶቼ ነበሩት።

“በተጫዋችነት ዘመኔ አላሳካሁትም በማለት የምቆጭበት ነገር የለም። የአንድ ተጨዋች ስኬቱ እስከ ብሔራዊ ቡድን መጫወት እና በነበረባቸው ክለቦች ዋንጫዎችን ማሸነፍ ነው። እንደኔ እንግዲህ በጨዋታ ዘመኔ ተደስቼ እና ስኬታማ ሆኜ ነው ያሳለፍኩት። ይቆጨኛል የምለው ነገር የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከተባሉ አማካዮች እና አጥቂዎች ጋር በክለብም በብሔራዊ ቡድንም አብሬ ተጫውቻለው። ይሄም በራሱ ስኬት ነው ብዬ እወስደዋለው።

“ዮርዳኖስ ‘ቡሎ’ የሚል ቅፅል ስም አለው። የሚገርመው ግን እኔ ምንም ቅፅል ስም የለኝም። ስምዖን ዓባይ ብቻ ነው መጠርያዬ (ፈገግ እያለ)

“በተጫዋችነት ዘመኔ ብዙ ገጠመኞች ይኖራሉ። አንድ የማልረሳው ግን መብራት ኃይል እያለው አልጄሪያ ላይ ጄ ኤስ ካቢላ ከሚባል ክለብ ጋር እየተጫወትን የማዕዘን ምት አገኘን። አንድ በጣም ረጅም እና ግዙፍ ተካላካይ ነበራቸው። ኮርናውን ለመግጨት ወደዛ ወደዚህ ስል ገርሞት ያየኛል። ‘ከኔ በላይ ዘሎ ሊመታ ነው ?’ ዓይነት ነገር። ኳሱ ሲሻማ መለያዬን እና እኔን ከጎን በአንድ እጁ ያዘኝ። ወዴት ልሂድ ? መንቀሳቀስ አልቻልኩም። ኳሱ ካለፈ በኋላ ወረወረኝ። ልዩነታችን በጣም ነው የገርመኝ (እየሳቀ)። በንቀት ነው ያየኝ ሁሉ። በእኛ እና በእነሱ መካከል ያለውን ልዩነት ስለሚያስታወኝ ሁሌ ሳስበው ይገርመኛል።

“የአሰልጣኝነት ህይወት አጀማመሬ 1997 ላይ የቡና ደጋፊዎች ተስፋ ለኢትዮጵያ የሚባል ቡድን አቋቁመው ነበር፤ ካሳዬ አሰልጣኝ የነበረበት። የመጀመሪያ ደረጃ ኮርስ ከወሰድኩ በኋላ ከእሱ ጋር ነበር የጀመርኩት። ካሳዬ በመሀል አሜሪካ በሄደበት ጊዜም ለሦስት ዓመት ቡድኑን ይዤ ቆይቼ ነበር። ከዚያ በኋላ ቡድኑ በበጀት ችግር ምክንያት ሳይቀጥል ሲቀር ወደ መብራት ኃይል ተስፋ ቡድን ሄጃለው። መብራት ኃይል ድሬዳዋ ፣ መቐለ እና ሀዋሳ ላይ ፕሮጀክቶች ስለነበሩት የድሬዳዋው ላይ መስራት ችያለው። በመቀጠል በናሽናል ሲሚንት ተስፋ ቡድን በማሰልጠን እንዲሁም በቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ አገልግያለው። በናሽናል ሲሚኒት የሰብስቤ እና የወርቁ ደርገባ ምክትል ሆኜ እየሰራው በየመሀሉም በዋና አሰልጣኝነት የሰራሁባቸው ወቅቶች ነበሩ። ቀጥሎም በድሬዳዋ ፖሊስ ከአሰልጣኝ አምሀ ጋር ሰርተን ነበር። ከዛ በኋላ ነው 2009 ላይ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ሲመጣ የእሱ ምክትል ሆኜ ድሬዳዋ ከተማ የመጣሁት። ሁለተኛው ዓመት ላይ እሱ ባለመግባባት ክለቡን ሲለቅ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ይዤ ነበር። እንዲሁ ከሌሎች አሰልጣኞች ጋርም በምክትልነት እየሰራው ቆይቼ ዐምና ደግሞ በዋና አሰልጣኝነት እስከ ግማሽ ድረስ መሄድ ችዬ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን የተወሰነ ዕረፍት ማድረግ ፈልጌ ነበር። በዛውም ኮቪድ በመግባቱ ምንም እንቅስቃሴ አልነበረም። ነገር ግን ከአንድ ወር ወደዚህ ከአንዳንድ ክለቦች ጋር ንግግሮችን ጀመሪያለው። ውጤቱን እንግዲህ በቀጣይ የምናየው ይሆናል።

“አሁኑ ያለው የድሬዳዋ የእግርኳስ ደረጃ ትኩረት አልተሰጠውም እንጂ የተሰጥኦ ምንጩ አልደረቀም። የኢትዮጵያ ውድድሮች ቀንሰዋል። በፕሪምየር ሊጉም ወደ ምስራቁ ክፍል ያለው ተሳታፊው ድሬዳዋ ከተማ ብቻ ነው። ድሮ እኛ በወጣንበት ጊዜ ውድድሮች በየክልሉ ነበሩ፤ ወደ ስምንት የሚሆኑ ቡድኖችም ነበሩ። ወደ ተለያዩ ክለቦች የመግባት እና የተለያዩ ተጫዋቾችን እያዩ ለማደግ ዕድሉ ነበር። በየቀበሌው በየሰፈሩ ውድድሮች ነበሩ። መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶት የነበረ ነገር ነው። አሁን ግን ትኩረቱ ያለው ድሬዳዋ ከተማ ነው። ናሽናል ሲሚንትም ፈርሷል ፤ የከተማው ክለብ እና ፖሊስ ብቻ ናቸው ያሉት። በፕሮጀክት ታቅፈው ደቻቱ፣ እኛም ሠፈር፣ ለገሀሬ ፣ ሳቢያን አሉ ከልጅነታቸው የሚሰሩ። ነገር ግን የት ድረስ ነው የሚሄዱት የሚለውን ስናይ በጣም የተገደበ ነው። አንድ ክለብ ብቻ ነው ያለው፤ ትኩረትም አልተሰጣቸውም። በየቀበሌው በየሰፈሩ የነበረው ውድድር አሁን ቀርቷል። ልጆቹ እርስ በእርስ ነው የሚጫወቱት እንጂ የፉክክር መንፈስ ያለው ነገር የለም። በኛ ጊዜ በስፖርት ኮሚሽንም የተሻለ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር። የተለያዩ ክለቦችም ነበሩ፤ ‘C’ አለ ‘B’ አለ። ብዙ አማራጭ ነበር። እና አሁንም ትኩረት አለመሰጠቱ እንጂ በየሠፈሩ ተሰጥኦ ያላቸው ብዙ ልጆች አሉ።

“ለቀድሞው ተጫዋቾች ትኩረት አለመሰጠቱ በድሬዳዋ እግርኳስ ላይ ተፅዕኖ አድርጓል ብዬ ገምታለሁ። በተለያየ ጊዜ ተጫዋች የነበሩ አሁን ሜዳ ላይ የቀሩ አሉ። በቅርብ እነሱን ለማስታወስ የተጀመሩ ነገሮች ይኑሩ እንጂ ‘ነብይ በሀገር አይከበርም’ እንደሚባለው ነው። ለድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም የለፉ ብዙ ሰዎች አሉ። እነርሱን የማስታወስ ነገር እኛ ጋር በጣም ደካማ ነው። ሌላው ቢቀር ያ ሰው ያለበት ቦታ ላይ ሄዶ ምስጋና ማቅረብ እና ዕውቅና መስጠት በራሱ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል። ስንት ታሪክ የሰሩ የተለያዩ ተጫዋቾች እኮ መንገድ ላይ ወድቀው ታመው ሞተዋል። አሁንም ያ ነገር መደገም የለበትም። እነዚህ ሲከበሩ ነው ታች ያሉት ተስፋ የሚኖራቸው። በቅርቡ አሁን አሁን በወጣቶች የተጀመረ እንቅስቃሴ አለ። ነገር ግን በመስተዳደር ደረጃ ጠንከር ብሎ ቢያዝ መልካም እንደሆነ አስባለሁ።

“የንግግር ክህሎቴን ያዳበርኩት የውጪ ኳሶችን በጣም እከታተላለሁ። ኳሱን ብቻ ሳይሆን ከጨዋታዎች በኋላ አሰልጣኞች የሚሰጡትን አስተያየት እከታተላለው። ተረጋግተው የሚናገሩ አሉ ፣ በጣም ስሜታዊ የሚሆኑም አሉ ፤ እነዛን ነገሮች በትኩረት እከታተላለው። ከእነርሱ ጥሩ የሆኑትን ነገሮች እወስዳለው። ከዛ በተጨማሪ አባቴ ‘በሁሉ ነገር ላይ ተረጋጋ’ ይለኛል። ለመናገርም መረጋጋት ያስፈልጋል። ካልተረጋጋህ የማይሆኑ ነገሮችን ተናግረህ ከራስክም ሰዎች ጋር ልትጋጭ ትችላለህ። በጨዋታ ወቅት ላይ ያልተረጋጋሁ በጣም ቆነጥናጣ ብሆንም ከጨዋታ በኋላ ግን ተረጋግቼ ሀሳቤን ለመስጠት ከብዙ አሰልጣኞች ከሀገራችንም ጭምር ትምህርት ወስጃለሁ።

“ተጫውቶ ላለፈ ሰው አሰልጣኝነት በጣም በጣም ይከብዳል። ተጫውተህ ማለፍህን አስቦ ህዝቡ ብዙ ይጠብቅብሀል። ‘እንዴት ለሱ አይታየውም?’ ብሎ ሁሉ ያስባል። በእርግጥ የተጫወተ ብቻ አሰልጣኝ ይሆናል የሚል ህግ የለም። ዋናው መማር እና ዕውቀቱን መያዝ ነው። ተጫውቶ ማሳለፉ የሚሰጥህ ነገር ቢኖርም እኔ በግሌ ‘ያልተጫወተ ማሰልጠን አይችልም’ የሚለውን ሀሳብ አልቀበለውም። በአጠቃላይ ተጫውተህ ስታሰለጥን ብዙ ስለሚጠበቅብህ ከፍተኛ ጫና አለው።

“በኛ ጊዜ የነበረው እና አሁን ያለውን የእግርኳስ ደረጃ ለማነፃፀር ሁለቱም እንደየዘመኑ ነው። እኛ ስንጫወት ለአፍሪካ ዋንጫ አላለፍንም ፤ የተገደበ ነበር አካሄዳችን። በጣም ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ቢኖሩም ረጅም ርቀት መሄድ አልተቻለም። አሁን ግን ከ31 ዓመት በኋላ ማለፍ ተችሏል። ያ በዚህ ዘመን ላሉት አንድ ስኬት ነው። በሌላ በኩል ያኔ ቴክኒክ ሙሉ የሆኑ ተጫዋቾችን ዓይነት በዚህ ዘመን ግን ማግኘት ከባድ ነው። ከዚህ አንፃር በውጤት ይሄኛው፣ በተጫዋች ጥራት ደግሞ የቀደመው ጊዜ የተሻሉ ናቸው ማለት ይቻላል።

“የቤተሰብ ህይወቴ አግብቻለሁ፤ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ልጆች አሉኝ። ልጆቼ ቅዱስ እና ሀሴት ፤ ባለቤቴ አርሴማ ትባላለች። ትልቁ ልጄ 15 ትንሿ ደግሞ 3 ዓመታቸው ነው። ወንዱ ልጄ ኳስ ይመለከታል ክህሎቱም አለው እንጂ እንደኔ እና ዮርዳኖስ አባታችንን ስናይ የነበረን ዓይነት ነገር አይታይበትም። እኔም ትምህርቱ ላይ እንዲያተኩር ብዙ አልጫነውም። በእርግጥ ተጫዋች ቢሆንልኝ ደስ ይለኛል ፤ ወደፊት የምናየው ይሆናል።

“በመጨረሻ ኢትዮጵያ ውስጥ እግር ኳሱን ለማሳደግ በብዙ መልኩ መሰራት አለበት ብዬ አስባለው። በተጨዋቾች እና በአሰልጣኞች ላይ ብዙ መሰራት አለበት። ማንም ሰው መመዘን ያለበት በሥራው ነው። ‘ምን ሰራ? ምን ውጤት አመጣ ?’ ነው መባል ያለበት። ከክለብ ያለው ነገር ወደ ብሔራዊ ቡድን ይሄዳል። የክለብ አካሄድ እና ሥራ ትክክል ካልሆነ ብሔራዊ ቡድን ላይ የተስተካከል ነገር መጠበቅ ከባድ ነው። ክለቦች አካባቢ ያሉ ችግሮች ግልፅ በሆኑ አሰራሮች መስተካከል አለባቸው። በሄድኩባቸው ክለቦች ካየኋዋቸው ችግሮችም አንፃር ነው። እነዛን ነገሮች ካስተካከልን ጠንካራ ነገር መገንባት እንችላለን ብዬ አስባለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!